በደቡብ ክልል በርካታ ሰዎች “ከህግ ውጭ” ታስረው እንደሚገኙ ኢሰመጉ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን በርካታ ሰዎች “ከህግ ውጪ በእስር ላይ እንዳሉ” ማረጋገጡን አስታወቀ። በተያዘው መጋቢት ወር ብቻ፤ ከደቡብ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች “ግድያ፣ እስር እና የመብት ጥሰቶች” መፈጸማቸውን ኢሰመጉ ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ይህን ያስታወቀው “አስቸኳይ ትኩረት የሚሹ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች” በሚል ርዕስ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 13፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። የዛሬው የኢሰመጉ መግለጫ በአራት ክልሎች ያሉ የሰብአዊ መብት ሁኔታዎችን የዳሰሰ ሲሆን፤ አብዛኛውን ቦታ የሰጠው በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ተከስተዋል ላላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ነው።   

በጋሞ ዞን፣ በቁጫ ወረዳ፣ ጋሌ ሞጎላ ከተማ 15 ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ የጠቀሰው ኢሰመጉ፤ በወረዳው ውስጥ በሚገኙት ቁጫ አልፋ እና ሰላም በር በተሰኙ ሁለት ከተሞች “በርካታ ሰዎች” ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በፖሊስ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም ገልጿል። በቁጫ ወረዳ ስር ባሉ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ፤ በርካታ ሰዎች ከህግ ውጪ በእስር ላይ እንዳሉ ኢሰመጉ ባገኛቸው መረጃዎች ለማረጋገጥ መቻሉንም አስታውቋል።

የተቋሙ መግለጫ በደቡብ ክልል በሚገኘው የአማሮ ልዩ ወረዳ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንም ተመልክቷል። ኢሰመጉ “የሸኔ ታጣቂዎች” ሲል የጠራቸው ኃይሎች፤ በአማሮ ልዩ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች በተለያዩ ጊዜያት በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን በመግለጫው ጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም በርካቶች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም አትቷል። 

“በአካባቢው ያለው ችግር አሁንም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ ከዲላ ወደ አማሮ የሚወስደው መንገድ ከተዘጋ ከወር በላይ እንደሆነው እና ከቡሌ ሆራ ወደ አማሮ ኬሌ የሚወስደው መንገድም በቅርቡ በሸኔ ታጣቂዎች መዘጋቱን ኢሰመጉ ካገኛቸው መረጃዎች ማረጋገጥ ችሏል” ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በመግለጫው አስፍሯል። በአማሮ እና በአጎራባቹ ኮንሶ ዞን ላሉት ችግሮች በመንግስት በኩል “በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ዘላቂ መፍትሔ ባለመቅረቡ” የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአካባቢዎቹ አሁንም ቀጥለው እንደሚገኙ አብራርቷል። 

ኢሰመጉ በዛሬው መግለጫው ያነሳው ሌላው ጉዳይ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ነው። በክልሉ በምስራቅ ወለጋ ዞን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታስረው የነበሩ ሰዎች እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አመልክቷል። 

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ ባለፈው ሳምንት አርብ መጋቢት 9፤ 2014፤ የተፈጸሙ ጥቃቶችንም ኢሰመጉ በመግለጫው አካትቷል። በፈንታሌ ወረዳ “የሸኔ ታጣቂዎች” ፈጽመውታል ባለው ጥቃት በርካታ ወጣቶች መገደላቸውን የመብት ተሟጋች ተቋሙ ገልጿል። በአምቦ ወረዳ “ማንነታቸው ባልታወቁ ቡድኖች” በተመሳሳይ ቀን በተፈጸመ ጥቃት ደግሞ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመጉ አስታውቋል።    

በአዲሱ ደቡብ ምዕራብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞንም ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ አንድ ወጣት “በአሰቃቂ ሁኔታ ማንነታቸው ባልታወቁ ቡድኖች መገደሉን” ኢሰመጉ በመግለጫው አንስቷል። ተደጋጋሚ ጥቃት እና ግጭቶች በሚስተዋሉበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል እና ንብረት ማውደም ተባብሰው መቀጠላቸውን የገለጸው ኢሰመጉ፤ ይህ ሁኔታ “በከፍተኛ ደረጃ ያሳስበኛል” ብሏል። 

ኢሰመጉ በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፤ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን “በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ እንዲሁም የዜጎችን በህይወት የመኖር እና የአካል ደህንነት መብቶችን እንዲያስከብሩ” ጥሪውን አቅርቧል። በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ እና ኮንሶ ዞን ባሉ አንዳንድ ወረዳዎች በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች፤ የሚመለከታቸው የፌደራል እንዲሁም የደቡብ ክልል መንግስት አካላት “ዘላቂ መፍትሔን እንዲሰጡ” አኢሰመጉ በተጨማሪነት ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)