የመከላከያ ሰራዊት የቆቦ ከተማን መልቀቁን መንግስት አስታወቀ

የመከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘውን የቆቦ ከተማ ለቅቆ መውጣቱን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ። መከላከያ ሰራዊቱ በትግራይ ክልል አቅራቢያ የምትገኘውን ቆቦ ከተማን የለቀቀው “የህዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል” መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል። 

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 21፤ 2014 ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የህወሓት ቡድን “የተለመደውን የሰው ኃይል ማዕበልን በመጠቀም የቆቦን ከተማ በብዙ አቅጣጫ እያጠቃ ነው” ሲል ከስሷል። ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት “አሸባሪ” ሲል የጠራው የህወሓት ቡድን፤ “በከተማ ውስጥ ሰርጎ ገቦችን በማስረግ የከተማ ውስጥ ውጊያ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል” ሲል ወንጅሏል።

ህወሓት “የህዝብን ደህንነት አደጋ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ” በሚያደርገው በዚህ እንቅስቃሴ ምክንያት፤ የመከላከያ ሰራዊት “ወደ ኋላ መጥቶ ለመከላከል የሚያስችለውን ወታደራዊ ይዞታዎች” ለመያዝ “መገደዱን” የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል። የህወሓት ኃይል “የትግራይን ወጣት እየማገደ በህዝብ ማዕበል ማጥቃቱን ካላቆመ” የመከላከያ ሰራዊት “ሕጋዊ ፣ ሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታውን ለመወጣት የሚገደድ ይሆናል” ሲልም የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)