በጋምቤላ ከተማ በነበረ ውጊያ፤ 50 ሲቪል ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ  

በሃሚድ አወል

በጋምቤላ ከተማ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደ ውጊያ፤ የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች 50 ሲቪል ሰዎች መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማን “ለመቆጣጠር ሙከራ አድርገው ነበር” የተባሉት የ“ኦነግ ሸኔ” እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ታጣቂዎች ደግሞ ሰባት ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። በተኩስ ልውውጥ ወቅት በየትኛው አካል እንደተገደሉ ያልታወቁ ስድስት ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውንም ይፋ አድርጓል።  

ኢሰመኮ ይህን የገለጸው በወቅቱ በጋምቤላ ከተማ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 18፤ 2014 ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርት ነው። ኮሚሽኑ በዚሁ ሪፖርቱ፤ ሰኔ 7፤ 2014 በጋምቤላ ከተማ የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ፤ ኢሰመኮ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ምርመራ ሲያደርግ እንደነበር አስታውቋል። 

ከሰኔ 20 ጀምሮ ሲደረግ በቆየው በዚሁ ምርመራ፤ ኢሰመኮ ከ58 ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጉን በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል። ቃለ ምልልሶቹ የተካሄዱት ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከዓይን እማኞች እና “ሌሎች ምስክሮች” ጋር መሆኑን ጠቁሟል። በምርመራውም “ ‘የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሳሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሣሪያ አውጡ’ በሚል ምክንያት” የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች 50 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን ከዓይን እማኞች እንዳረጋገጠ አስታውቋል።

የጸጥታ ኃይሎቹ በሲቪል ሰዎቹን ላይ የመግደል እርምጃ የወሰዱት፤ በጎዳናዎች፣ በመኖሪያ ቤት ግቢዎች ውስጥ እና በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ አካባቢ መሆኑን በኢሰመኮ ሪፖርት ተመልክቷል። በዚህ ሁኔታ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች ውስጥ  ሴቶች እና የአእምሮ ህመምተኞች እንደሚገኙበት በሪፖርቱ ሰፍሯል። 

“ኮሚሽኑ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከነዋሪዎች እና ከዓይን እማኞች በሰበሰበው መረጃና በሌሎች ማስረጃዎች፤ በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት ሲቪል ሰዎች አስክሬን፤ በክልሉ ልዩ ኃይሎች እና መደበኛ ፖሊሶች በጭነት መኪና ተሰብስቦ ወዳልታወቀ ቦታ እንደተወሰደ እና በጅምላ እንዲቀበሩ የተደረገ መሆኑን እንዲሁም አስክሬን እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ የሟች ቤተሰቦችም መከልከላቸውን አረጋግጧል” ሲል ዛሬ ይፋ የተደረገው ሪፖርት አትቷል። 

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ “አስክሬን ይሰጠን” ብሎ ለፖሊስ ኮሚሽኑ ያመለከተ የከተማዋ ነዋሪ አለመኖሩን ለኢሰመኮ መግለጹ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ሆኖም “በየመንገዱ የነበሩ አስክሬኖች በከተማው ማዘጋጃ ቤት ተሰብስበው መቀበራቸውን” ማረጋጡን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። ኢሰመኮ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ለጋምቤላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርብም፤ ከመስሪያ ቤቱ “የፌደራል ፖሊስን አነጋግሩ” የሚል ምላሽ ማግኘቱን ገልጿል። 

በጋምቤላ ከተማ ተፈጽሟል ስለተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስመልክቶ ኢሰመኮ ለፌደራል ፖሊስም ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር በሪፖርቱ አመልክቷል። ለዚሁ የኮሚሽኑ ጥያቄ የፌደራል ፖሊስ የምዕራብ መምሪያ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ከውጊያው በኋላ ያደረገውን ማጣራት ተንተርሶ መረጃ እና ምላሽ መስጠቱን ኢሰመኮ አስታውቋል። የፌደራል ፖሊስ  ጋምቤላ ቅርንጫፍ በዚሁ ምላሹ “የክልሉ ልዩ ኃይሎች በተለይ ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም በከተማው በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ መረዳቱን” ገልጿል ተብሏል።

ሰኔ 7፤ 2014 በጋምቤላ ከተማ የነበረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ የክልሉ መንግስት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የጋምቤላ ከተማን ለመቆጣጠር ሙከራ ካደረጉት የጋምቤላ ነጻነት ግንባር እና “ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጉን አስታውቆ ነበር። በዚሁ የተኩስ ልውውጥ 17 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የክልሉ መንግስት መግለጹ ይታወሳል። 

በዕለቱ በጋምቤላ ከተማ በነበረው ውጊያ “ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት” የደረሰባቸው ሰዎች ብዛት 25 መሆኑን ኢሰመኮ በምርመራ ሪፖርቱ ላይ ገልጿል። ከጸጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ “በርካታ ሰዎች ላይ የመደብደብ እና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን” ማረጋገጡንም ኮሚሽኑ ገልጿል። ከግድያ እና ከአካል ጉዳት በተጨማሪ የ“ኦነግ ሸኔ” እና ጋነግ ታጣቂዎች፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች፤ በሲቪል ሰዎች ንብረት ላይ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸማቸውንም ኢሰመኮ አክሏል። 

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በምርመራ ሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ ስድስት ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል። የመጀመሪያው ምክረ ሀሳብ በሲቪል ሰዎች ላይ ከህግ ውጭ ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳቶችን እና የንብረት ዘረፋዎችን የፈጸሙ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ ተባባሪ ወጣቶች እና ይህንን ድርጊት ሲመሩ የነበሩ ኃላፊዎች ላይ “አስፈላጊ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ” የሚያሳስብ ነው። 

ኮሚሽኑ ከዚህ በተጨማሪም ለሟቾች ቤተሰቦች፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈላቸው እና የስነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ጠይቋል። የጋምቤላ ክልል መንግስት የተገደሉ ሲቪል ሰዎች የተቀበሩበትን ቦታ ለቤተሰብ እንዲያሳውቅ እና አስክሬኖች ለቤተሰቦች የሚመለሱበት እንደዚሁም በክብር የሚቀበሩትበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ኢሰመኮ በምክረ ሀሳቡ ላይ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግስት ተመሳሳይ ጥሰቶች በጸጥታ ኃይሎች እንዳይፈጸሙ እንዲያረጋግጡ ኢሰመኮ በተጨማሪነት ጠይቋል። ሁለቱ አካላት፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንዲከላከሉ እና የሰዎችን ደህንነት እንዲያስጠብቁም ኢሰመኮ አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)