በሃሚድ አወል
ከሁለት ሳምንት በፊት “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል” የተከሰሱት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ደራሲ አሳዬ ደርቤ እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ፤ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 3፤ 2015 ከእስር ተለቀቁ። ከሁለቱ ተከሳሾች ጋር በአንድ መዝገብ ክስ የተመሰረተበት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ግን በፍርድ ቤት የተጣለበትን የጉዞ እግድ የተመለከተ ሰነድ ለፖሊስ ባለመቅረቡ ሳይፈታ መቅረቱን ጠበቃው አቶ አዲሱ አልጋው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ሁለቱ ተከሳሾች ዛሬ ከቀኑ አስር ሰዓት ተኩል ገደማ የተለቀቁት፤ በአዲስ አበባ ገነት ሆቴል አቅራቢያ ከሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሆነ የጋዜጠኛ መዓዛ ባለቤት አቶ ሮቤል ገበየሁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መዓዛ እና አሳዬ ከእስር የተፈቱት፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋስትና ከተፈቀደላቸው ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ የወንጀል ችሎት፤ ባለፈው ሳምንት አርብ መስከረም 27፤ 2015 በዋለው ችሎት ለሶስቱ ተከሳሾች የፈቀደው ዋስትና ተፈጻሚ ባለመሆኑ ጠበቆቻቸው ለችሎቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር። አቤቱታውን የተመለከተው ችሎቱ፤ የፌደራል ፖሊስ የሽብር ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮሚሽነር ተስፋዬ አሽኔ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ እና ተከሳሾቹን እንዲፈቱ፤ የማይፈቱበት ምክንያት ካለም ቀርበው እንዲያስረዱ ለዛሬ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
በፍርድ ቤቱ ጥሪ የተደረገላቸው ኮሚሽነር ተስፋዬ ዛሬ ችሎት ቀርበው ባለማስረዳታቸው፤ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በነገው ዕለት ችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ችሎቱ ሌላ ትዕዛዝ መስጠቱን ከተከሳሾች ጠበቃ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በአንድ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ፣ ጎበዜ ሲሳይ እና ደራሲ አሳዬ ደርቤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር። “ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራችና ባለቤት የሆነችው መዓዛ እና “የአማራ ድምጽ” የሚል ስያሜ ያለውን የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን ያቋቋመው ጋዜጠኛ ጎበዜ በፖሊስ የተያዙት በተመሳሳይ ቀን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጷጉሜ 3፤ 2014 ነበር።
ሌላኛው ተከሳሽ አሳዬ ደርቤ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው፤ ከሁለቱ ጋዜጠኞች መታሰር ሁለት ቀናት በኋላ በዋለው የአዲስ ዓመት በዓል በሚከበርበት መስከረም 1፤ 2015 ነው። በተለያየ የምርመራ መዝገብ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የነበሩት ሶስቱ ተጠርጣሪዎች፤ ከሶስት ሳምንት ቆይታ በኋላ “የሃሰት ወሬን በመንዛት፤ በውጊያ ውስጥ የወገን ጦር አሰላለፍና ቦታን ለጠላት እና ለህዝብ በመሳወቅ” በሚሉ ወንጀሎች በዐቃቤ ህግ ክስ ቀርቦባቸዋል።
በዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ በአንደኛነት የተጠቀሰው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ሶስት ክሶች ሲቀርብበት፤ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሽነት በተመዘገቡት አሳዬ ደርቤ እና መዓዛ መሐመድ ላይ የቀረበው አንድ ክስ ብቻ ነው። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ አምስት የሰነድ እና ሁለት የገላጭ ማስረጃዎችን አያያዞ ማቅረቡ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
በክስ ሰነዱ ላይ ከተዘረዘሩ የሰነድ ማስረጃዎች ውስጥ ሶስቱ አንደኛ ተከሳሽ የሆነውን ጎበዜ ሲሳይን የሚመለከቱ የፌደራል ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ ውጤት እና “የፌስቡክ ድረ ገጽ ፖስት” ናቸው። ቀሪዎቹ ሁለት ማስረጃዎች ደግሞ ከመከላከያ ሚኒስቴር በተለያዩ ቀናት የተጻፉ ደብዳቤዎች መሆናቸው በክስ ሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።
ዐቃቤ ህግ “ገላጭ ማስረጃ” ብሎ ከዘረዘራቸው ሁለት ማስረጃዎች ውስጥ አንዱ በ“ሮሃ ሚዲያ” አማካኝነት ለእይታ የበቃ ቃለ ምልልስ ነው። በጋዜጠኛ መዓዛ እና በደራሲ አሳዬ መካከል የተካሄደው ይህ ይህ ቃለ ምልልስ፤ በቅርቡ ለንባብ በበቃው የደራሲው መጽሐፍ እና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነበር። በፌደራል ዐቃቤ ህግ በሁለተኛነት የቀረበው “ገላጭ ማስረጃ”፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ “አማራ ፔሪስፔክቲቭ” የትዊተር ስፔስ ላይ ቀርቦ ያደረገውን ንግግር የተመለከተ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)