ነባሩ የደቡብ ክልል ስያሜውን እና አደረጃጀቱን ለመቀየር የህገ መንግስት ማሻሻያ ሊያደርግ ነው

– የነባሩን ክልል መጠሪያ ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ለመቀየር ምክረ ሃሳብ ቀርቧል

በአማኑኤል ይልቃል

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስያሜውን እና አደረጃጀቱን ለመቀየር የሚያስችለውን የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለጸ። የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ የታቀደው፤ በመጪው ጥር ወር ከሚደረግ ህዝበ ውሳኔ በኋላ ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል በነባሩ ክልል ላይ “መሰረታዊ ለውጥ” ስለሚያስከትል ነው ተብሏል።  

በነባሩ ደቡብ ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች፤ ራሳቸውን ችለው በክልል ለመደራጀት ያቀረቡት ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተቀባይነት ያገኘው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ውስጥ ነበር። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወቅቱ ያሳለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ለጥር 29፣ 2015 ቀነ ቀጠሮ ይዟል። 

የነሐሴውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ተከትሎም፤ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ እና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ተግባር ማስፈጸሚያ ጽህፈት ቤት” በዚያውኑ ወር ተቋቁሟል። ይህ ጽህፈት ቤት፤ አዲስ የሚመሰረተው ክልል ሊኖሩት የሚችሉትን መዋቅሮች እና በነባሩ ክልል ላይ የሚፈጠሩ መሰረታዊ ለውጦችን አጥንቶ ለውይይት የማቅረብ ስራን የመምራት ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በዚህም መሰረት የነባሩ ደቡብ ክልል ህገ መንግስትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሰነዶች፤ የህግ ባለሙያዎችን በያዘ ቡድን እየተዘጋጀ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኑርዬ ሱሌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በቡድኑ ውስጥ ጉዳዩ “የሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅሮች” ተወካዮች እንደተካተቱበትም አክለዋል። 

የአዲሱ ክልል ምስረታ፤ የነባሩን ክልል ስያሜ፣ መቀመጫ፣ ሰንደቅ ዓላማ እና የህዝብ መዝሙርን የተመለከቱ “መሰረታዊ ለውጦች” እንደሚያስከትል ያስረዱት አቶ ኑርዬ፤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ማስተካከያ የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግን ግድ እንደሚል አስረድተዋል። “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል” የሚለው የነባሩ ክልል መጠሪያ ቀደም ሲል በውስጡ የነበሩትን ብሔረሰቦች እና ህዝቦች “በሚመጥን መልኩ” መውጣቱን የሚገልጹት የጽህፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ፤ ስያሜውን በቀጣይ የሚኖረውን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

አሁን ራሱን የቻለ ክልል የሆነው የሲዳማ ዞን ከነባሩ ክልል በህዳር 2012 ዓ.ም. በህዝበ ውሳኔ ከመነጠሉ በፊት፤ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በ17 ዞኖችና ሰባት ልዩ ወረዳዎች የተዋቀረ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ፤ በነባሩ ክልል ስር የሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን” መስርተዋል።  

በመጪው ጥር መጨረሻ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ህዝበ ውሳኔ ደግሞ፤ ነባሩ ክልል ተጨማሪ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ያጣል። አብዛኛዎቹ መዋቅሮች ከክልሉ ሲወጡ የሚፈጠሩ ለውጦችን በተመለከተ የሚሰራው ስራ “ለዛሬ ለነገ ተብሎ የሚቀመጥ አይደለም” የሚሉት አቶ ኑርዬ፤ በዚህም ምክንያት እርሳቸው በምክትል ስራ አስኪያጅነት የሚመሩት ጽህፈት ቤት አዲሱን ክልል የመመስረት እና ነባሩን ክልል የማስቀጠል ስራዎችን “ጎን ለጎን” እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በነባሩ ክልል ውስጥ የሚቀጥሉ የክልል፣ የዞንና ልዩ ወረዳ አመራሮች ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ፣ “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል” የሚለውን መጠሪያ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ወደሚለው እንዲቀየር ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውን አቶ ኑርዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ያቀረበውን ይህን ምክረ ሃሳብ በተመለከተ፤ በሁሉም ደረጃ ከሚገኙ የነባሩ ክልል አመራሮች ጋር ባለፈው ማክሰኞ ህዳር 20፣ 2015 በቡታጅራ ከተማ ውይይት መካሄዱን ምክትል ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። 

“የስያሜ ማሻሻያ በሚደረግበት ጊዜ ‘ማዕከላዊ ኢትዮጵያ’ የሚል ስያሜ ይሁን [የሚለውን]፤ እንደ አመራር የተግባባንበት ነው” ሲሉ ምክረ ሃሳቡ የክልሉ አመራሮች የተስማሙበት መሆኑን አቶ ኑርዬ አስረድተዋል። በቡታጅራ ለተደረገው ውይይት የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ  እና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል፤ የነባሩ ክልል ህገ መንግስት ማሻሻያ የሚደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ነሐሴ ባደረገው ስብሰባ ያሳለፈውን ውሳኔ ተንተርሶ ነው ይላሉ። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነባሩን ክልል አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ “ራሱን በአዲስ በመቀየር በአንድ ክልል ተደራጅቶ ይቀጥል” የሚል መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ስንታየሁ፤ አዲሱን “የደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለማደራጀት የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ ነባሩን ክልል ለማስቀጠል እንደሚተገበሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሂደቱም “በአንድ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት” እንደሚመራ አስረድተዋል። ቀጣይ ሂደቱን በተመለከተ ደግሞ “ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ አልቆ፤ የሁለቱም ክልሎች ምስረታ በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ነው የሚሆነው” ብለዋል።   

የነባሩን ክልል ህገ መንግስት ማሻሻል፤ በእርግጥም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስመልክቶ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተረፈ በዳዳ ጥያቄ አቅርባ ነበር። ዳይሬክተሩ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በነሐሴ ወር መጨረሻ ባደረገው ስብሰባ ላይ ዋነኛ ጉዳይ የነበረው አዲስ ክልል የመመስረት እና ነባሩን የማስቀጠል አጀንዳ እንደነበር አስታውሰዋል። 

“በፌዴሬሽን ምክር ቤት የታየው የስም ጉዳይ አይደለም” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የክልሉን ስያሜ እና አደረጃጀት የመቀየር ጉዳይ የክልሉ ምክር ቤትን የሚመለከት እንደሆነ አስረድተዋል። አክለውም “ስማቸውን rebrand ለማድረግ የሚከለክል ህግ የለም። ስልጣናቸው ነው” ሲሉ ውሳኔው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን የነባሩ ክልል እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

የነባሩን የደቡብ ክልል ህገ መንግስት የማሻሻል ስራ የሚከናወነው፤ በክልሉ ህገ መንግስት ላይ ይህንኑ በተመለከተ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ተፈጻሚ በማድረግ መሆኑን የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጁ አቶ ኑርዬ ተናግረዋል። የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፤ የራሱን ህገ መንግስት ሲያሻሽል የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። 

የደቡብ ክልል የመጀመሪያ ህገ መንግስት የጸደቀው በሰኔ 1987 ዓ.ም ነበር። ለሰባት ዓመት ገደማ ያገለገለው ይህ ህገ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻሻለው በህዳር 1994 ዓ.ም ነው። የደቡብ ክልል ምክር ቤት በወቅቱ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ያሻሻለው ህገ መንግስት፤ በአስራ ሁለት ምዕራፎች እና በ128 አንቀጾች የተዋቀረ ነበር። በግንቦት 2000 ዓ.ም.  ለሁለተኛ ጊዜ የተሻሻለው የክልሉ ህገ መንግስት የቀረበለት የደቡብ ክልል ምክር ቤት፤ በአራት አንቀጾች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አጽድቋል።   

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ህገ መንግስትን የማሻሻል ሃሳብ ለውይይት የሚቀርበው፤ በክልሉ ምክር ቤት ወይም በብሔረሰቦች ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ አብላጫ ድምጽ ሲጸድቅ ነው። በክልሉ ከሚገኙት የዞን እና የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ውስጥ በአንድ ሶስተኛ የሚሆኑት የህግ መንግስት ማሻሻያ ሃሳቡን በአብላጫ ድምጽ ካጸደቁት፤ ውይይት ሊደረግበት እንደሚችል ተደንግጓል። 

የህግ መንግስት ማሻሻያን ተቀብሎ ለማጽደቅ፤ የክልሉ ምክር ቤት እና የብሔረሰቦች ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የጋራ ስብሰባው ለማሻሻያው በሁለተኛ ሶስተኛ አብላጫ ድምጽ ድጋፍ የሚሰጥ ከሆነ፤ ጸድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን በክልሉ ህግ መንግስት ላይ ተቀምጧል። የህገ መንግስት ማሻሻያው ተቀባይነት የሚያገኘው፤ በክልሉ ከሚገኙ የዞን እና የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ሲያጸድቁት መሆኑ በህገ መንግስቱ ሰፍሯል።  

የህገ መንግስት ማሻሻያ ስለሚደረግበት ሂደት የሚያትተው የክልሉ ህገ መንግስቱ ክፍል፤ ሶስት አይነት ማሻሻያዎች እንዳሉ ይዘረዝራል። የመጀመሪያው፤ የማሻሻያ አንቀጹ ራሱን ማሻሻልን የሚመለከት ነው። ሁለተኛው፤ የህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆዎችን የያዘውን ምዕራፍ ሁለት እንዲሁም መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን የያዘው ምዕራፍ ሶስት እንዴት እንደሚሻሻሉ የሚደነግግ ነው። ሶስተኛው፤ ከእነዚህ ውጪ ያሉ የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች የሚሻሻሉበትን አካሄድ የሚያትት ነው።  

ነባሩ የደቡብ ክልል አሁን ሊያደርግ ያሰበው ማሻሻያ፤ የክልሉን ስያሜ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር፣ የስራ ቋንቋ እና ርዕሰ ከተማን የተመለከቱ አንቀጾችን የያዘውን የህገ መንግስቱን ምዕራፍ አንድን የሚመለከት እንደሆነ አቶ ኑርዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስያሜን የተመለከተው የህገ መንግስቱ ክፍል፤ የክልሉ መጠሪያ “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል” የሚል እንደሆነ ደንግጓል።   

በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ፤ ከላይ ሰማያዊ፣ በመሐሉ ነጭ እና ከታች ቀይ ሆኖ መሐሉ ላይ የክልሉ ዓርማ የሆነው ጎጆ ይኖረዋል። የደቡብ ክልል መዝሙር፤ የክልሉን ህገ መንግስት ዓላማዎች እና የክልሉ ህዝቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በዲሞክራሲ ስርዓት አብሮ ለመኖር ያላቸው እምነት የሚካተትበት እንደሆነ በህገ መንግስቱ ላይ ተቀምጧል። መዝሙሩ የክልሉን ህዝብ የወደፊት የጋራ ዕድል የሚያንጸባርቅ መሆን እንዳለበትም በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል። 

በደቡብ ክልል የሚገኙ ቋንቋዎች በመንግስት ዘንድ እኩል ዕውቅና እንደሚኖራቸው የሚያስረዳው የህገ መንግስቱ ክፍል፣ የክልሉ መንግስት የስራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ ደንግጓል። በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ግን የየራሳቸውን የስራ ቋንቋ በየምክር ቤቶቻቸው ሊወስኑ እንደሚችሉ በዚሁ ክፍል ላይ ተመልክቷል። የደቡብ ክልል ርዕሰ ከተማን የሚመለከተው ክፍል፤ የክልሉን መንግስት መቀመጫነት የሰጠው ለአዋሳ ከተማ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)