በወላይታ ዞን በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ፤ “የህግ ጥሰት ፈጽመዋል” ተብለው የተጠረጠሩ 92 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአማኑኤል ይልቃል

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ “የህግ ጥሰት ፈጽመዋል” ተብለው የተጠረጠሩ፤ 92 የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የወረዳ እና የቀበሌ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ። በተመሳሳይ ድርጊት የተጠረጠሩ ሌሎች 44 ሰዎች መጥሪያ ወጥቶባቸው እየተፈለጉ እንደሆነም ተገልጿል።

የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን” ለመመስረት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ህዝበ ውሳኔ የተካሄደው፤ የወላይታ ዞንን ጨምሮ በነባሩ የደቡብ ክልል ስር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ነበሩ። በወላይታ ዞን በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ፤ በመራጮች ምዝገባ ሂደት እና ድምጽ በተሰጠበት ወቅት “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች አግኝቻለሁ ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት ወር አስታውቆ ነበር። 

በወላይታ ዞን የተፈጸመው ጥሰት “የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት እና እውነተኝነት ያሳጣ እና አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱንም የሚያዛባ ነው” ያለው ምርጫ ቦርድ፤ በዚህም ምክንያት በዞኑ የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። ቦርዱ ከዚህ በተጨማሪ  በህዝበ ውሳኔው ወቅት የተፈጸሙት “አብዛኛዎቹ” ጥሰቶች በህግ የሚያስጠይቁ በመሆናቸው፤ የፌደራል ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲያደርግ እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ደብዳቤ እንደሚልክ አስታውቆ ነበር፡፡ 

ይህንን ተከትሎ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከደቡብ ክልል መንግስት የተውጣጣ የምርመራ ቡድን፤ በወላይታ ዞን ተሰማርቶ ማጣራት ሲያካሄድ መቆየቱን የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎአ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ የምርመራ ቡድን፤ ጉዳዩን ለመከታተል የወላይታ ዞን ካቋቋመው የምርመራ ቡድን ጋር ለአንድ ወር ያህል በጥምረት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም  ኃላፊው ገልጸዋል። የጋራ ምርመራ ቡድኑ በምርጫ ቦርድ ጥቆማ በተሰጠባቸው 357 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ማጣራት ማድረጉንም አክለዋል።

ምርጫ ቦርድ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔን ለማካሄድ፤ በወላይታ ዞን ያደራጃቸው የምርጫ ጣቢያዎች አጠቃላይ ብዛት 1,112 ነበር። ይህም በነባሩ ደቡብ ክልል ህዝበ ውሳኔውን ካካሄዱ መዋቅሮች ውስጥ፤ በርካታ ምርጫ ጣቢያዎችን በመያዝ የወላይታ ዞን ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ ማድረጉ ይታወሳል። በዞኑ ህዝበ ውሳኔውን የማስተባበር ሚና የነበራቸው ስምንት ማዕከላት በምርጫ ቦርድ ተቋቁመው ነበር። 

ቦርዱ ከህዝበ ውሳኔው መጠናቀቅ በኋላ ከእያንዳንዱ ማዕከላት 25 በመቶ ጣቢያዎችን በናሙናነት ወስዶ ባደረገው ምርመራ፤ በአብዛኛዎቹ ላይ “ከፍተኛ የሆነ ጥሰቶች እና ግድፈቶችን” ማግኘቱን ማስታወቁ አይዘነጋም። በዚህ መነሻ ላይ ተመስርቶ በወላይታ ዞን የተሰማራው የፌደራል እና የክልል ምርመራ ቡድን ባደረገው ማጣራት፤ ተጠርጣሪዎችን ለይቶ ማጠናቀቁን የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ገልጸዋል።

ከህዝበ ውሳኔውን ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የህግ ጥሰቶች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስራ የማዋል ስራም፤ ካለፈው ሳምንት ሰኞ መጋቢት 25፤ 2015 አንስቶ ሲከናወን መቆየቱን አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል። “አሁን 92 የሚሆኑ በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ አሉ። ፍርድ ቤት አውቆ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆ በቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው” ሲሉ ኃላፊው ስለ ተጠርጣሪዎቹ አስረድተዋል። 

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ ቀሪዎቹ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች አመራሮች እንደሆኑ ጠቁመዋል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ከነበሩት አመራሮች መካከል የተወሰኑት “የምርጫ ህግን አልፈው ወደ ምርጫ ክልል ገብተዋል” ተብሎ መረጃ የመጣባቸው መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል። ሌሎች አመራሮች ደግሞ “የምርጫ መዝገብ ይዘው ተገኝተዋል” የሚል መረጃ የቀረበባቸው እንደሆኑ አክለዋል።

የጋራ ምርመራ ቡድኑ በቁጥጥር ስር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ “የማስረጃ ምዘና የማካሄድ እና የማጠቃለያ ስራዎችን” በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የወላይታ ዞን የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አስታውቀዋል። የምርመራ ቡድኑ ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ባልተያዙ 44 ተጠርጣሪዎች ላይ፤ ከፍርድ ቤት መጥሪያ አስወጥቶ ፍለጋ እያካሄደ መሆኑንም አክለዋል። 

በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ በድጋሚ ከመካሄዱ በፊት የህግ ተጠያቂነት መስፈን እንዳለበት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ከአንድ ወር በፊት በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር። “የህግ ተጠያቂነት ሳይታይ እንደገና ብንደግመው፤ ምናልባት ተመሳሳይ ጥሰት ያጋጥማል” ሲሉም የቦርድ ሰብሳቢዋ ስለ ሂደቱ አስፈላጊነት በወቅቱ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)