የአማራ ክልል ወደ መደበኛ ፖሊስ የሚገቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትን በተለያዩ “ዞኖች መድቦ እያንቀሳቀሰ” መሆኑን አስታወቀ   

በሃሚድ አወል

የአማራ ክልል “ወደ መደበኛ የክልል ፖሊስ ስራ እንገባለን” ያሉ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትን፤ በክልሉ ወደሚገኙ ዞኖች መድቦ እያንቀሳቀሰ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ ተናገሩ።  “በመደናገር” ወደ ተለያዩ አካባቢዎች “የተበተኑ” የልዩ ኃይል አባላትን የሚያሰባስቡ ግብረ ኃይሎች በዞን እና ወረዳ ደረጃ መቋቋማቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።

ዶ/ር ሰማ ይህን የገለጹት፤ በአማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ትላንት ረቡዕ ሚያዚያ 4፤ 2015 በሰጡት መግለጫ ነው። ዶ/ር ሰማ በአራት ቀናት ውስጥ በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡ፤ ሶስተኛው የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን ናቸው። ካለፈው እሁድ ወዲህ በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት ሌሎቹ ባለስልጣናት፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ እና የክልሉ  ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ናቸው። 

ሁለቱ ባለስልጣናት እንደሰጧቸው መግለጫዎች ሁሉ የትላንቱ የዶ/ር ሰማ ማብራሪያም፤ የክልል ልዩ ኃይሎችን “እንደገና ለማደራጀት” በፌደራል መንግስቱ የተወሰነው ውሳኔ እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ዋና ትኩረቱን ያደረገ ነበር። የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ የተላለፈው ውሳኔ “በሁሉም ክልሎች እየተፈጸመ ነው” ያሉት ዶ/ር ሰማ፤ “ይሄ ባለበት ሁኔታ የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል ብቻ ባለበት እንዲቆይ ማድረግ፣ ወደ ፌደራል ጸጥታ ተቋማት እንዳይገባ መከልከል የሚቻል አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

የአማራ ክልል ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ባደረገበት ወቅት፤ በሁለት ምክንያቶች “ችግሮች” ማጋጠማቸውን ዶ/ር ሰማ በትላንቱ ማብራሪያቸው አንስተዋል። ዶ/ር ሰማ ለችግሮቹ መፈጠር በቀዳሚነት የጠቀሱት፤ ከክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ጋር “ቀድሞ ውይይት ተደርጎ፣ በቂ መግባባት በማድረግ ረገድ፣ የተፈጠረ ክፍተትን” ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ ዶ/ር ሰማ “ብጥብጥ እና አመጽ በማስነሳት ስርዓት የመቀየር ፍላጎት ያላቸው” ሲሉ የገለጿቸው “ኃይሎች” ፈጠሩት ያሉት “የውሸት ፕሮፓጋንዳ” ነው። 

በዚህ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት “የተበተኑ” የልዩ ኃይል አባላት መኖራቸውን የአማራ ክልል የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪው ገልጸዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ፤ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ነበር። አቶ ግርማ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው “ጥቂት የተደናገጡ ክፍለ ጦሮች፤ በተለይ ደግሞ ለከተሞች ቅርብ የነበሩ ክፍለ ጦሮች ተደናግጠው ተበትነዋል” ብለው ነበር። 

እነዚህን “ተደናግጠው” እና “በመደናገር” ተበተኑ የተባሉትን የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የሚያሰባስብ ግብረ ኃይል፤ በክልሉ ስር በሚገኙ ወረዳ እና ዞኖች እንዲቋቋም መደረጉን ዶ/ር ሰማ በትላንቱ ማብራሪያቸው አስታውቀዋል። “ቀደም ሲል በመደናገር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቀድመው ወደተለያዩ አካባቢዎች የተበተኑ የልዩ ኃይሎችን በሚመለከት፤ በየአካባቢው፣ በየወረዳው፣ በየዞኑ እና በየፖሊስ ጣቢያው ይሄን የሚያሰባስብ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው” ሲሉ ስለ ግብረ ኃይሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በአብዛኛዎቹ” ወረዳዎች ግብረ ኃይሉ መቋቋሙን ያነሱት ዶ/ር ሰማ፤ ኮሚቴ ያላቋቋሙ ዞኖች እና ወረዳዎችም ኮሚቴ አቋቁመው የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትን “የመሰብሰብ ስራ እንዲሰሩ” አሳስበዋል። ዶ/ር ሰማ ለዞኖች እና ወረዳዎች ከሰጡት ማሳሰቢያ በተጨማሪ ለልዩ ኃይል አባላትም ጥሪ አቅርበዋል። ዶ/ር ሰማ በዚህ ጥሪያቸው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተበተኑ የልዩ ኃይል አባላት፤ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው እንዲመዘገቡ እና “ወደ ቀጣይ ተልዕኮ” እንዲሰማሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ የክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደ ፍላጎታቸው ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም የክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችሉ አስታውቆ ነበር። እነዚህን የልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩንም በወቅቱ መግለጹ አይዘነጋም።

ዶ/ር ሰማ በትላንቱ ማብራሪያቸው፤ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መካከል “ወደ መደበኛ ፖሊስ ስራ እንገባለን” በሚል ፍላጎታቸውን ላሳወቁ የጸጥታ ኃይሎች ምደባ ተከናውኖ ስምሪት መጀመሩን ይፋ አድርገዋል። “የክልሉን የጸጥታ መዋቅር ለማጠናከር ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎች ወደ ሁሉም የክልላችን ዞኖች አካባቢ መድበን እያንቀሳቀስን  ነው” ያሉት የአማራ ክልል የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ፤ እነዚህ የልዩ ኃይል አባላት “በአብዛኛው ዞኖች” ደርሰውም አቀባበል እንደተደረገላቸው ጨምረው አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)