የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ሂደት ቅሬታ ቀረበበት   

በሃሚድ አወል

የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ “የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ የምርጫ ሂደት” ነው አለ። የጋራ ምክር ቤቱ “በበርካታ ምርጫ ጣቢያዎች እና ምርጫ ክልሎች ከመራጮች ምዝገባ ሂደት ጀምሮ የህግ ጥሰቶች ተፈጽመዋል” ሲል ሂደቱን ተችቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የጋራ ምክር ቤቱ የህግ ጥሰት ተፈጽሟል ከማለቱ በፊት ቦርዱ የህግ ጥሰቶች መፈጻማቸውን በክትትል እና ቁጥጥር ማረጋገጡን እና ጥሰት በተፈጸመባቸው ምርጫ ጣቢያዎችም የድጋሚ ምዝገባ ማድረጉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።

የዞኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የህዝበ ውሳኔውን ሂደት የተቸው ከዘጠኝ ቀናት በኋላ የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 20፤ 2015 በአዲስ አበባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። አስር የፖለቲካ ፖርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የዞኑ ምክር ቤት “ይህ ህዝበ ውሳኔ ህዝቡ ለመምረጥ የሚፈልገውን አማራጭ ያላቀረበ በመሆኑ፤ የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ የምርጫ ሂደት እንደሆነ ተገንዝበናል” ብሏል፡፡

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ እስራኤል ካሳ “ህዝቡ የሚፈልገው አማራጭ እንደ አማራጭ ስላልተካተተ፤ አብዛኛው ሰው ካርድ አልወሰደም። የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ ቅሬታውን እየገለጸ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የወላይታ ማስተባበሪያ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ እስራኤል አክለውም “ይህን ቅሬታ ለመሸፈን ሲባል በህገ ወጥ መንገድ ካርድ ሲታደል ነበር” ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ለጋዜጠኞች ባሰራጨው ሁለት ገጽ መግለጫ ላይም ይህ የሰብሳቢው ሀሳብ ተነስቷል። መግለጫው “መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ሳይመጡ በስማቸው በቀበሌ አመራሮች እና በአካባቢ የህግ አስከባሪዎች በኩል የምርጫ ካርዶች ወጪ ተደርገዋል” ሲል ወንጅሏል።

የህግ ጥሰቶቹ አስቀድመው መታወቃቸውን የገለጸው የምርጫ ቦርድ ኮሚዩኒኬሽን ክፍል፤ በወላይታ ዞን “የህግ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል በተባሉት ምርጫ ጣቢያዎች ድጋሚ ምዝገባ ማካሄዱን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። ቦርዱ ከሶስት ሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአጠቃላይ ለህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ከተካሄደባቸው ከ3,769 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ24ቱ “ከፍተኛ የሆነ የህግ እና የአፈጻጸም ጥሰት” እንደተፈጸመባቸው አስታውቆ ነበር።

የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የዛሬው መግለጫ ሌላኛው ትኩረት የህዝበ ውሳኔ አማራጮችን ከማስተዋወቅ ጋር የተያያዘ ነው። ምክር ቤቱ በመግለጫው “ህዝበ ውሳኔ ላይ ለምርጫ የሚቀርቡት ምልክቶች ለማህበረሰቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ማስተዋወቅ ሲገባ፤ አንድን ምልክት ብቻ የማስተዋወቅ ተግባር” እንዳለ ጠቅሷል።

አቶ እስራኤል “ህዝቡ ለምርጫ የቀረበው ሁለተኛው አማራጭ ምን እንደሆነ አያውቅም። አንድ አማራጭ ነው የቀረበው። እያስተዋወቁ ያሉት ነጭ እርግብን ነው” ሲሉ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። “የጎጆ ምልክትን ያለበትን አማራጭ እኔ አስተዋውቃለሁ ብሎ ኃላፊነት የሚወስድ ሰው ስለሌለ፤ ሁለተኛው አማራጭ ተደብቋል” ሲሉ የዞኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው ገልጸዋል። 

ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በመጪው ጥር 29 ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ፤ በአንድ ክልል መደራጀታቸውን ለሚደግፉ መራጮች ነጭ እርግብ፤ ለማይደግፉ ደግሞ የጎጆ ቤትን በምልክትነት አቅርቧል። ለዚህ ህዝበ ውሳኔ በድምሩ 3.02 ሚሊዮን መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት የተመዘገቡት በወላይታ ዞን መሆኑን የቦርዱ መረጃ ያሳያል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)