ስለ አቶ ደመቀ መኮንን ስንብት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ምን አሉ?

በተስፋለም ወልደየስ

ዛሬ ረፋዱን በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ፤ ላለፉት 32 ዓመታት በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች የሰሩት አቶ ደመቀ መኮንን፤ በመንግስት አስፈጻሚነት ከነበራቸው ስልጣን በይፋ ተሰናብተዋል። በስብሰባው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በኢፌዲሪ መንግስት ስም ምስጋና እንዲያቀርብላቸው” በጠየቁት መሰረት የፓርላማ አባላቱ ረዘም ያለ ደማቅ ጭብጨባ ለግሰዋቸዋል።

አቶ ደመቀ ላለፉት 11 ዓመታት የያዙትን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን፤ ዛሬ ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ አስረክበዋል። ላለፉት አራት ዓመታት ደርበው ሲሰሩ የቆዩትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት ቦታ ደግሞ በአንድ ወቅት በመስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ አጽቀስላሴ ተረክበዋቸዋል።

አቶ ደመቀ ከኃላፊነታቸው የተሸኙት በብልጽግና ፓርቲ “በነበረው የመተካካት አሰራር መሰረት” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። በፓርቲም ሆነ በመንግስት የነበራቸውን ስልጣን “በክብር እና በፍቅር” ያስረከቡት፤ እርሳቸው ራሳቸው “ላሳደጉት እና ለመሩት ሰው” መሆኑንም አብይ ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት የፓርቲ ስልጣን፤ በብልጽግና ፓርቲ አቶ ደመቀ የነበራቸውን የምክትል ፕሬዝዳትነትን ቦታ ነው። ገዢው ፓርቲ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ፤ አቶ ደመቀ የነበራቸውን የምክትል ፕሬዝዳንትነት ኃላፊነት ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ ማስረከባቸው የሚታወስ ነው። 

“በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መረካከብ እና ኢትዮጵያን ላገለገሉበት ‘እናመሰግናለን’ ተብሎ መሄድ ተጨማሪ ክብር መሆኑን እያንዳንዱ ሰው ማወቅ አለበት” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። “አሁን የሚደረገውን ነገር እያደረግን ያለነው፤ ተመካክረን፣ ተወያይተን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ስልጣን በሰላማዊ መንገድ በንግግር፣ በምክክር ብቻ የሚገኝ እንዲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም ባህል አድርገን መስራት ይኖርብናል” ሲሉ አሳስበዋል። 

“ብዙ አሉባልታ እና ወሬ በውጪ ቢሰማም፤ ሁሉም ነገር በምክክር፣ በውይይት፣ በመግባባት፤ በእያንዳንዱ መድረክ በሙሉ ድምጽ እያጸደቅን የመጣን መሆኑን ከግምት እንዲገባ [እጠይቃለሁ]” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።  ወደፊት እርሳቸው እና ሌሎችም መሰል ዕድልን እንዲያገኙ፤ የፓርላማ አባላት “በየእምነታቸው እንዲጸልዩላቸው” ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)