አቶ ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

– አምባሳደር አቶ ታዬ አጽቀስላሴ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ መቅደስ ዳባ ደግሞ የጤና ሚኒስትርን ሹመት አግኝተዋል

በተሰፋለም ወልደየስ

ላለፉት ሶስት ዓመታት የደህንነት መስሪያ ቤትን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ተሾሙ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ታዬ አጽቀስላሴ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የዓለም ጤና ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ረዳት የሆኑት ዶ/ር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

አቶ ተመስገን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን የያዙት፤ ላለፉት 11 ዓመታት በዚሁ የኃላፊነት ቦታ የቆዩትን አቶ ደመቀ መኮንንን በመተካት ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት የቀረበው የአቶ ተመስገን እና የሁለቱ ሚኒስትሮች ሹመት፤ ዛሬ ሐሙስ ጥር 30፤ 2016 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የጸደቀው በአብላጫ ድምጽ ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ወር ዕረፍት ከመበተኑ አንድ ቀን አስቀድሞ በተካሄደው በዚሁ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ፤ ሶስቱም ተሿሚዎች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እየተመሩ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። አቶ ተመስገን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን የያዙት፤ ላለፉት 11 ዓመታት በዚሁ የኃላፊነት ቦታ የቆዩትን አቶ ደመቀ መኮንንን በመተካት ነው።

የዛሬውን ሹመት ተከትሎ አቶ ተመስገን፤ “የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ የመስራት ስልጣን” በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን የኃላፊነት ቦታ በይፋ ተረክበዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ስልጣን በሕገ መንግስቱ መሰረት የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነት የሚሾም ግለሰብ፤ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው የሚሰጡትን ተግባሮች ከማከናወን” የዘለለ ስልጣን በሕገ መንግስቱ አልተሰጠውም።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ የሚሾም ግለሰብ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑም በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ተደንግጓል። ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “የቅርብ ሰዎች” ከሚባሉት አንዱ የሆኑት አቶ ተመስገን፤ ከእርሳቸው ጋር በሲቪል እና ወታደራዊ የተለያዩ ስራ ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት ሰርተዋል። አቶ ተመስገን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ዕውቂያ የሚጀምረው፤ ሁለቱም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ “በመረጃ ባለሙያነት” በሚሰሩበት ወቅት ነው። 

አዲሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ሻለቅነት ማዕረግ በደረሱበት የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ፤ በመረጃ ዋና መምሪያ፣ ኤሌክትሮኒክስ መምሪያ እና ቴክኒካል መረጃ መምሪያ ስር እንዳገለገሉ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምስረታ ወቅት ከነበሩ አመራሮች መካከል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ዛሬ ምክትላቸው ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ስማቸው ይነሳል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያውን ካቢኔያቸውን በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ሲያዋቅሩ፤  ኢንሳን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ አቶ ተመስገንን ሾመዋቸው ነበር። ሜጀር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይን በመተካት ወደ ቀድሞ መስሪያ ቤታቸው በኃላፊነት የመጡት አቶ ተመስገን፤ በኢንሳ የቆዩት ለስድስት ወራት ገደማ ብቻ ነበር።

በጥቅምት 2011 ዓ.ም. አብይ ለተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ሹመት ሲሰጡ፤ አቶ ተመስገን በሚኒስትር ማዕረግ  የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪነት ቦታን አግኝተዋል። ከአቶ ተመስገን አስቀድሞ ይህን የአማካሪነት ቦታ ይዘው የነበሩት፤ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው።

አቶ ተመስገን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከርም ቢሆን ከ10 ወራት በላይ አልዘለቁም። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና ሌሎች ሁለት ከፍተኛ አመራሮች በሰኔ 2011 ዓ.ም. መገደላቸውን ተከትሎ፤ አቶ ተመስገን ክልሉን የመምራት ኃላፊነት ከአንድ ወር በኋላ ተረክበዋል። በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ብቸና፣ ልዩ ስሙ ወይራ በተሰኘ አካባቢ የተወለዱት አቶ ተመስገን፤ ለክልሉ ሹመት አዲስ አይደሉም።

የተወለዱበትን ዞን በዋና አስተዳዳሪነት ከመምራት አንስቶ እስከ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ድረስ ተጉዘዋል።  የአማራ ክልል መንገዶች ባለስልጣንን በምክትል ስራ አስኪያጅነት፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲን ደግሞ በዋና ስራ አስኪያጅነት አገልግለዋል። በአንድ ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የጸጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪም ነበሩ።

አቶ ተመስገን በሐምሌ 2011 ዓ.ም. በተሾሙበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት የዘለቁት ለአንድ ዓመት ከሶስት ወር ብቻ ነው። በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ጦርነት ሲቀሰቀስ ግን ከክልል መሪነታቸው ተነስተው፤ የፌደራሉን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተሹመዋል። በዚሁ የኃላፊነት ቦታቸውም ላይም እስከ ዛሬው ዕለት ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)