ኢትዮጵያ ከፓሪስ ክለብ አበዳሪ ሀገራት ያገኘችው የዕዳ ክፍያ እፎይታ፤ ለተጨማሪ ጊዜያት ይራዘማል ብላ እንደምትጠብቅ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ። ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ተስፋቸውን የገለጹት፤ የኢትዮጵያ “ይፋዊ አበዳሪዎች” የሰጡት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት በቀረው በዚህ ጊዜ ነው።
የፓሪስ ክለብ ሀገራት ኢ-መደበኛ ስብስብ፤ ተበዳሪዎች ለሚገጥማቸው የዕዳ አከፋፈል እክል፤ ስርዓት ያለው ዘላቂ መፍትሔ የማመቻቸት ሚና ያለው ነው። በዚህ ኢ-መደበኛ ስብስብ ውስጥ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 22 ሀገራት ተካትተዋል።
የፓሪስ ክለብ ሀገራት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ጋር ከስምምነት ላይ እስክትደርስ ድረስ፤ በ2023 እና በ2024 መክፈል ለነበረባት የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እፎይታ የሰጧት ባለፈው ህዳር ወር ነበር። ለብድር እፎይታው የተቀመጠው ቀነ ገደብ የሚያበቃው መጋቢት 22፤ 2016 የነበረ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ከስምምነት ላይ ባለመድረሱ ለተጨማሪ ወራት ተራዝሟል።
በመጪው እሁድ ሰኔ 23፤ 2016 የሚያበቃው ቀነ ገደብ በድጋሚ የመራዘም ተስፋ እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ትላንት ሰኞ በፓርላማ በነበረ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ጥቆማ ሰጥተዋል። ዶ/ር እዮብ ስለዚህ ጉዳይ ያነሱት፤ የውጪ ብድር የእፎይታ ጊዜን በተመለከተ ከፓርላማ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።
ቋሚ ኮሚቴው የፌደራል መንግስት ለ2017 ያዘጋጀው በጀት፤ የእዳ ክፍያ ሽግሽግን እና የእፎይታ ጊዜን ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን በተመለከተ ከሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ ጠይቋል። ዶ/ር እዮብ ለፓርላማ አባላቱ ባቀረቡት ማብራሪያ “በእጃችን የገባውን ሽግሽግ አካትተናል። ግን ተጨማሪ የዕዳ ሽግሽግ እና እፎይታ ደግሞ እንጠብቃለን” ብለዋል።
“ከዚህ የሚገኘው ቁጠባ (saving) ተጨማሪ የልማት አቅም ይዞ የሚመጣ ይሆናል። ይሄን በየደረጃው ለምክር ቤት እያስታወቅን የምንሄድ ይሆናል” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል። የገንዝብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፈው ግንቦት ወር ለፓርላማ ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በተሰጣት የብድር እፎይታ ምክንያት መክፈል የነበረባትን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ለሌላ ጊዜ እንደተራዘመላት አስታውቀው ነበር።
“በእጃችን የገባውን ሽግሽግ አካትተናል። ግን ተጨማሪ የዕዳ ሽግሽግ እና እፎይታ ደግሞ እንጠብቃለን”
– ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፤ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ
የገንዘብ ሚኒስትሩ በዚሁ የስራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው፤ በተጨማሪ 49 ሚሊዮን ዶላር የእዳ ክፍያ ላይ ድርድር እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀው ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ለ2017 ካዘጋጀው በጀት ውስጥ፤ ለዕዳ መክፍያ እንዲውል የመደበው 139.3 ቢሊዮን ብር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)