በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 229 ደረሰ 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ በትላንትናው ዕለት በደረሰ የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 229 መድረሱን የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። የአስክሬን ፍለጋው ዛሬ ለሊቱን እንደሚቀጥልም መምሪያው አስታውቋል። 

ድንገተኛ የመሬት ናዳው በጎፋ ዞን የደረሰው፤ ትላንት ሰኞ ሐምሌ 15፤ 2016 ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ ነበር። በወረዳው ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የአንድ ቤተሰብ ቤት ከትላንት በስቲያ ለሊት ከተናደ በኋላ፤ በውስጡ የነበሩ ሰዎችን ለማትረፍ ወደ ቦታው የሄዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ ማጋጠሙን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ኃላፊዋ “ከባድ የሆነ የመሬት መናድ” ሲሉ በጠሩት አደጋ”፤ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ንብረት መውደሙን አስታውቀዋል። እስከ ዛሬ ከሰዓት ድረስ በአደጋው 150 ሰዎች ህይወት ማለፉ በክልሉ መንግስት የተገለጸ ቢሆንም፤ ቁጥሩ በየሰዓቱ የሚለዋወጥ በመሆኑ “ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ አልተቻለም” ሲሉ ወ/ሮ ሰናይት ማምሻውን ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ አመልክተዋል። 

ፎቶ፦ የጎፋ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

የጎፋ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን አባይነህ፤ የሟቾቹ ቁጥር ማምሻውን 229 መድረሱን ገልጸዋል። በመሬት ናዳው ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ ሰማንያ አንዱ ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በአካባቢው የተሰማሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች ዛሬ ለሊቱን ተጨማሪ አስክሬኖችን የማፈላለግ ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ኃላፊው አክለዋል። 

አደጋው ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል የተወሰኑትን በትላንትናው ዕለት ማዳን መቻሉን ያስረዱት ኃላፊው፤ ካሁን በኋላ በህይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት እድል የተመናመነ መሆኑን አስረድተዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያዋቀረው “የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የሚሰጥ ቡድን”፤ በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አስረድተዋል። 

አስቸኳይ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው ይህ ቡድን፤ በአደጋው አካባቢ ያሉ ሌሎች ነዋሪዎችን ወደ ተሻለ ቦታ የማሸሽ እና ሌሎችንም መሰል ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ወ/ሮ ሰናይት ጨምረው ገልጸዋል። “የእህል እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን የማቅረብ ስራ፤ አሁን ርብርብ እየተደረገበት ይገኛል” ሲሉም በክልሉ በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት አብራርተዋል። 

ፎቶ፦ የጎፋ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ በአቶ አለማየሁ ባውዲ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በዛሬው ዕለት በስፍራው በመገኘት፤ ጉዳት የደረሰባቸውን የአካባቢውን ህዝቦች መጎብኘታቸውን እና ማጽናናታቸውን ወ/ሮ ሰናይት ጠቅሰዋል። የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አደጋው ከደረሰ ጀምሮ የሀዘን መግለጫዎችን በየፊናቸው ሲያወጡ መቆየታቸውንም አክለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ዛሬ ማምሻውን በአደጋው የተሰማቸውን “ጥልቅ ሀዘን” ገልጸዋል። አብይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በጎፋ ዞን የደረሰውን የመሬት ናዳ አደጋ ተከትሎ “የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል በአካባቢው ተሰማርቶ የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ” መሆኑን ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)