የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ ላይ እንዲመሰረት ያደረገው ውሳኔ እንዲሰረዝ ኢህአፓ ጠየቀ

በሙሉጌታ በላይ

የኢትዮጵያ መንግስት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት፤ “ዳግም እንዲያጤነው” እና “እንዲሰርዘው” የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ (ኢህአፓ) ጠየቀ። የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ለውጡ “የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ በማቃወስ”፤ ሀገሪቱን “ለከፋ ትርምስ ሊዳርግ ይችላል” ሲል ፓርቲው አስጠንቅቋል።

ፓርቲው ይህን ያለው፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 30፤ 2016 አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። መግለጫው በዋናነት ያተኮረው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ እና የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ለውጥ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት እንደተሸጋገረ” የገለጸው ሐምሌ 22፤ 2016 ነበር። ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ዶላርን የሚገዛበት የውጭ ምንዛሬ ተመን፤ ከ57 ብር ከ50 ሳንቲም በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ 95 ብር ከ69 ሳንቲም አሻቅቧል። በአንዳንድ የግል ባንኮች የአንድ ዶላር የመግዢያ ተመኑ በዛሬው ዕለት 100 ብር ደርሷል። 

ብሔራዊ ባንክ አዲሱን የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት “በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች” እንደሚያስገኝ ቢገልጽም፤ በዛሬው የኢህአፓ መግለጫ ግን ተደጋጋሞ የተነሳው ግን ተቃራኒው ነው። የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በንባብ ባሰሙት የፓርቲው መግለጫ፤ “እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ደካማ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ሀገሮች የገንዘብ የውጭ ምንዛሬ ዋጋን ማንሳፈፉ ቀርቶ፤ መቀነስ እንኳን ይጎዳቸዋል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

“የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን” የተደረገው፤ ሀገሪቱ “በጦርነቶች፣ ድርቅ፣ መፈናቀሎች፣ በቀጠናዊ ነውጦች ሁኔታ” ውስጥ ባለችበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው በፓርቲው መግለጫ ተነስቷል። “የገዢው ፓርቲ ፓሊሲዎች አካሄድ በጦርነት መር አስተሳሰብ በተዛባበት ሁኔታ፤ የብር የውጭ ምንዛሬ የማንሳፈፍ እርምጃ” መወሰዱ “አደገኛ እርምጃ” መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል። 

በዚህ ምክንያት “የሚመጣው ጥፋት ከፍተኛ” መሆኑን በመግለጫው ያሳሰበው ኢህአፓ፤ ውሳኔውን ያሳለፈው መንግስት “ቆም ብሎ እንዲያስብ” ጠይቋል። የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር “የብልጽግና መንግስት ዳግም ቆም ብሎ እንዲያስብ፤ የወሰነውን ውሳኔ እንዲያጤነው እና እንዲሰርዘውም ጭምር ነው ኢህአፓ የሚጠይቀው። አለዚያ በዚህ ድፍረት፣ ህዝቡ ምን ያመጣል በሚል ንቀት የሚሄድ ከሆነ ግን በአጭር ጊዜያቶች የሚታዩ ብዙ ችግሮች ይኖራሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

“የብልጽግና መንግስት ዳግም ቆም ብሎ እንዲያስብ፤ የወሰነውን ውሳኔ እንዲያጤነው እና እንዲሰርዘውም ጭምር ነው ኢህአፓ የሚጠይቀው። አለዚያ በዚህ ድፍረት፣ ህዝቡ ምን ያመጣል በሚል ንቀት የሚሄድ ከሆነ ግን በአጭር ጊዜያቶች የሚታዩ ብዙ ችግሮች ይኖራሉ”

– የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ (ኢህአፓ)

ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ አዲሱን የፖሊሲ ለውጥ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫም ተመሳሳይ ሃሳብ አንጸባርቆ ነበር። ኢዜማ በዚሁ መግለጫው፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ መወሰኑ “በሀገር እና በህዝብ ላይ የምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል” ሊደርስ እንደሚችል አሳስቧል። ለዚህ ምስቅልቅል “መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድም” ፓርቲው መግለጹ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)