ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ሊያካሄድ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአሜሪካ ዶላር ለሚፈልጉ ባንኮች፤ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ሊያካሄድ ነው። ጨረታው ነገ ረቡዕ ነሐሴ 1፤ 2016 እንደሚካሄድ ባንኩ ዛሬ ባወጣው ማስታወቂያ ገልጿል። 

በ2000 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ባንኩ የውጭ ሃገር ገንዘቦችን የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም “ለመግዛት፣ ለመሸጥ እና ለመያዝ እንደሚችል” ይደነግጋል። ባንኩ ይህንን መሰረት በማድረግ በቅርቡ ያወጣው መመሪያ፤ ብሔራዊ ባንክ ህጋዊ እውቅና ላላቸው ባንኮች የውጭ ምንዛሬን በጨረታ ሊሸጥ እና ከእነርሱ ሊገዛ እንደሚችል አስፍሯል። 

ብሔራዊ ባንክ ይህን መሰሉን ጨረታ የሚያካሄደው፤ “በውጭ ምንዛሬ ገበያ ለሚታዩ የተዛቡ ሁኔታዎች” መፍትሔ ለማበጀት መሆኑ በመመሪያው ላይ ተቀምጧል። እንዲህ አይነት ጨረታዎች በውጭ ምንዛሬ ገበያ “ግልጽነት እና ገበያን መሰረት ያደረገ የዋጋ ትመናን ለማበረታታት” እንዲሁም በገበያው የሚፈጠሩ “መዛባት እና የቢሆን ግምቶችን (speculation) የመከላከል” አላማን ያነገቡ መሆናቸውንም መመሪያው ገልጿል።

በመመሪያው መሰረት ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የሚያካሄደው በአሜሪካ ዶላር እና በኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው። ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ያወጣው ማስታወቂያ፤ በአሜሪካ ዶላር የሚካሄድ ጨረታን የተመለከተ ነው። በዚህ ጨረታ መሳተፍ የሚሹ ባንኮች፤ የሚፈልጉትን የዶላር መጠን በጨረታ ማመልከቻቸው ላይ ማካተት እንዳለባቸው ባንኩ በማስታወቂያው ላይ አመልክቷል። 

ተጫራች ባንኮች አንድን ዶላር በምን ያህል ብር ለመግዛት እንደሚሹ፤ በጨረታ ማመልከቻቸው ላይ መጥቀስ እንዳለባቸውም በዛሬው ማስታወቂያ ላይ ተጠቁሟል። ብሔራዊ ባንክ በዚሁ ማስታወቂያው፤ ባንኮች ዶላር የሚሸጥላቸው ባቀረቡት ዋጋ ላይ በመመስረት መሆኑን አስታውቋል። 

ሆኖም ማንኛውም ባንክ ለጨረታ ከተዘጋጀው የዶላር መጠን ውስጥ ከ20 በመቶ የበለጠ ማግኘት እንደማይችል ባንኩ ገልጿል። ባንኮች ክፍያቸውን መፈጸም ያለባቸው ጨረታው በሚካሄድበት እለት መሆኑንም ብሔራዊ ባንክ አክሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገበያውን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ተመሳሳይ ጨረታዎችን በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ሊያካሄድም እንደሚችልም ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሯ” ቤርሳቤህ ገብረ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አደርጋለች]