የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስድስት ቢሊዮን ዶላር አዲስ አየር ማረፊያ ከሚያስገነባበት ቦታ፤ 2,500 አባወራዎች እንደሚነሱ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ተናገሩ። አየር መንገዱ ተነሺዎችን በሚያሰፍርበት ምትክ ቦታ ላይ፤ የመኖሪያ ቤት እና ለነዋሪዎቹ የሚያስፈልጓቸው “ፋሲሊቲዎች” እንደሚገነቡላቸውም ገልጸዋል።
አቶ መስፍን ይህን የገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ አዲስ የሚያስገነባውን የአየር ማረፊያ ንድፍ ለማሰራት፤ መቀመጫውን በዱባይ ካደረገ አማካሪ ኩባንያ ጋር ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ነው። ስምምነቱን ዛሬ አርብ ነሐሴ 3፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል የተፈራረሙት፤ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን እና የዳር አል-ሃንዳሳህ ኩባንያ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ታሪቅ ናጂ አል-ቃኒ ናቸው።
ዳር አል-ሃንዳሳህ የተሰኘው ኩባንያ፤ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በመገንባት ላይ ለሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የማማከር ስራ በማከናወን ላይ የሚገኝ ነው። የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ግንባታው ሲጠናቀቅ 100 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።
ኩባንያው የዲዛይን ስራውን የሚያከናውንለት እና በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ “አቡሴራ” በተባለ ቦታ የሚገነባው አዲስ አየር ማረፊያ፤ 100 ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው አቶ መስፍን በዛሬው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በዋነኛ ማዕከልነት እየተገለገለበት የሚገኘው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት፤ በዓመት 25 ሚሊዮን መንገደኞችን ወደ ማስተናገድ በቅርቡ እንደሚሸጋገርም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከ64 ዓመታት በፊት የተገነባው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 720 አውሮፕላኖች መግዛቱን ተከትሎ ነው። “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ” የሚል ስያሜ የነበረው ይህ አየር ማረፊያ፤ በተለያዩ ጊዜያት ማስፋፊያዎች ተደርገውለታል።
አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በአንድ ጊዜ ማስነሳት እና ማሳረፍ የሚችለው አንድ አውሮፕላን ብቻ እንደሆነ የገለጹት አቶ መስፍን፤ አዲስ የሚገነባው አየር ማረፊያ በአንጻሩ በአንድ ጊዜ አራት አውሮፕላኖች ለማስነሳት እና ለማሳረፍ የሚችሉ መንደርደሪያዎች እንደሚኖሩት ገልጸዋል። አየር ማረፊያው ግንባታው በአምስት ዓመታት ውስጥ ሲጠናቀቅ፤ ከአፍሪካ ትልቁ ኤርፖርት እንደሚሆን ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።
የአዲሱ አየር ማረፊያ ግንባታ “እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ” እንደሚችል የጠቆሙት አቶ መስፍን፤ ለዚሁ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማበደር ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩ ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ አዲስ አየር ማረፊያ እንደሚገነባ ይፋ ያደረገው፤ ከስድስት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)