የኢትዮጵያ መንግስት ለደመወዝ ጭማሪ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ እንደመደበ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርበው ተጨማሪ በጀት የሚካተተው የደመወዝ ጭማሪ በዋናነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችን የሚመለከት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ተሿሚዎች ብዙ ላያገኙ ይችላሉ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደመወዝ ጭማሪን ጉዳይ ያነሱት፤ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እና ከግል ባንኮች ፕሬዝዳንቶች ጋር በተደረገ ውይይት ነው። ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀው ውይይት፤ የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ቢሆንም በገበያ ላይ ወደ ተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት የተደረገው ሽግግር ዋነኛ ትኩረት አግኝቷል።
ከውይይቱ አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ ወስደው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “በስንት ልመና፣ በስንት ጭቅጭቅ የመጣ” ያሉትን “ድል”፤ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መያያዙ ቅር አሰኝቷቸው ታይቷል። ተሳታፊዎች ካቀረቧቸው ጥያቄዎች በኋላ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ምላሽ የሰጡት አብይ፤ የመንግስታቸውን ውሳኔ በተደጋጋሚ ሲከላከሉ ተደምጠዋል።

መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ካደረገው ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት አብረው መስራታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተበደሩትን የገንዘብ መጠን ጭምር ጠቅሰዋል። አብይ እንዳሉት ዘውዳዊው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት 300 ሺህ ዶላር፣ ደርግ በሁለት ፕሮግራሞች 14.8 ሚሊዮን ዶላር ኢህአዴግ በ3 ፕሮግራሞች 88 ሚሊዮን ዶላር ተበድረው ነበር።
ከእርሳቸው በፊት የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ከIMF ገንዘብ ሲበደር የብርን “58 በመቶ ዲቫሉዌሽን ሰርቶ” እንደነበር የተናገሩት አብይ፤ በወቅቱ ይፋዊው እና ትይዩው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተዋህደው ቢሆን ኖሮ “ይህ ሁሉ ስቃይ ዛሬ የለም” ብለዋል። ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር “በጣም የተሳካ የሚባል ድርድር ነው ያካሄድነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
አብይ እንዳሉት ከIMF ለኢትዮጵያ የተሰጠው ብድር፤ ንግድ ባንክን ከኪሳራ ለመታደግ የሚያስችል 700 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተካቶበታል። ዓለም አቀፉ ተቋም የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) የተባለውን ፕሮግራም በማጽደቁ፤ መንግስታቸው የ4.9 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በአበዳሪዎቹ እንደሚደረግለት ተናግረዋል።

አንዲያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጨረሻውን ውሳኔ ከኮሶ መድኃኒት ጋር አመሳስለውታል። “ጨካኞች አንዴ ይጨልጡና ያን መራራ ወስደው ኮሷቸው ይሽራል” ያሉት አብይ፤ በኢኮኖሚ ማሻሻያው “የሚጎዱ ሰዎች” መኖራቸውን አምነዋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው “በትሩን የሚያሳርፍባቸው” ካሏቸው መካከል የመንግስት ሰራተኞች እና ገበሬዎች ይገኙበታል።
ተጽዕኖውን ለመቋቋም መንግስታቸው ለሚያደርገው የደመወዝ ጭማሪ 90 ቢሊዮን ብር እንዳስፈለገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንቱ ገለጻቸው ጠቅሰዋል። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግስት ሰራተኞች የሚደረገው ጭማሪ “በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በወር 1,500 ብር ለሚከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች 300 ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው ለተገኙ ታዳሚያን ተናግረዋል። ከ25 ሺህ ብር በላይ ወርሃዊ ደመወዝ የሚከፈላቸውን የመንግስት ሰራተኞች “ለጊዜው ታገሰን አልንው” ሲሉም ተደምጠዋል። የደመወዝ ጭማሪው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ባገኘው ብድር እና እርዳታ የሚሸፈን ነው።
ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር የተገኘውን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ባለፈው ረቡዕ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያጸደቁት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ይህንኑ ያካተተ ተጨማሪ በጀት ለፓርላማ እንደሚቀርብ ገልጸው ነበር። ተጨማሪ በጀቱ ለዝቅተኛ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጭማሪ እንዲሁም ለነዳጅ፣ ለምግብ ዘይት፣ ለአፈር ማዳበሪያ እና ለመድኃኒት እንደሚውልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንቱ ማብራሪያቸው፤ የ2017 በጀት ዓመት “ከባድ ጊዜ ነው። መዘጋጀት ያስፈልጋል” ሲሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገሪቱን ሊፈታተን እንደሚችል ጠቁመዋል። “ይህን ዓመት ያንገጫግጨናል” ያሉት አብይ፤ “በትብብር ከተሰራ” የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለ10 ተከታታይ ዓመታት እንደሚያድግ ተስፋቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)