በቤርሳቤህ ገብረ
መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ገቢውን በ75 በመቶ ገደማ በማሳደግ 163.7 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ። ኩባንያው በተያዘው 2017 በጀት አመት፤ የደንበኞቹን ቁጥር በስድስት በመቶ በመጨመር 83 ሚሊዮን ለማድረስ ግብ ማስቀመጡንም ገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህን የገለጸው፤ የዘንድሮውን በጀት ዓመት እቅዱን በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 9፤ 2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የኩባንያው የ2017 እቅድ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እቅዱ መቃኘት ስለነበረበት ይፋ ለማድረግ ለቀናት መዘግየቱን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ላለፉት 130 ዓመታት የቴሌኮም አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በተያዘው ዓመት ገቢውን ባለፈው ዓመት ካገኘው በ74.7 በመቶ ለማሳደግ ማቀዱን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ 93.7 ቢሊዮን ብር ፤ በእቅድ ከያዘው 103.6 በመቶውም ያሳካ እንደነበር ባለፈው ሐምሌ መጀመሪያ በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
ኩባንያው የእዚህ ዓመት ገቢውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ታሳቢ ካደረጋቸው ማሻሻያዎች መካከል፤ “የገቢ ምንጭ ማስፋት” እና “የደንበኞች ቁጥር ማሳደግ” የሚሉት ይገኙበታል። ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ዓመት የሞባይል ስልክ አገልግሎት ደንበኞቹን በ5.5 በመቶ በማሳደግ ወደ 79.7 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ አቅዷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የሞባይል ዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ16 በመቶ በመጨመር 47.4 ሚሊዮን ለማድረስ ኩባንያው አቅዷል። “የፊክስድ ብሮድባንድ” ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ደንበኞቹን በ25 በመቶ ለማሳደግ ያቀደው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዓመቱ መጨረሻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎቹን ቁጥር ወደ 934 ሺህ ለማድረስ ተልሟል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የኩባንያቸውን የ2017 እቅድ ለማሳካት በአስቻይ ሁኔታነት ከጠቀሷቸው ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት እና መረጋጋት፣ የፋይናንስ እድገት ቀጣይነት፣ የተሻለ ጸጥታ እና ደህንነት የሚሉት ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)