በቤርሳቤህ ገብረ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 6፤2017 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ተመራጭ የሆኑትን የአቶ ዮሐንስ ተሰማን ያለመከሰስ መብት አነሳ። የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት የተነሳው፤ “ህዝብን በህዝብ ላይ የማነሳሳት ስራ ሰርተዋል”፣ “ሀሰተኛ መረጃዎችን አሰራጭተዋል”፣ “መንግስትን በኃይል ለመጣል ከሚጥሩ አካላት ጋር ግንኙነት አላቸው” በሚል ተጠርጥረው ነው።
የክልሉ ምክር ቤት የዛሬውን ውሳኔ ያሳለፈው፤ አቶ ዮሐንስ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር ከዋሉ አንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ነው። የቦዴፓው የምክር ቤት አባል፤ በክልሉ አድማ በታኝ ከመኖሪያ ቤታቸው የተወሰዱት ባለፈው እሁድ ከሰአት እንደነበር ባለቤታቸው እና የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መግለጻቸው ይታወሳል።
አቶ ዮሐንስ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው አስቀድሞ፤ የጉዞ እግድ እንደተጣለባቸው ተነግሯቸው ከኦሶሳ አየር ማረፊያ እንዲመለሱ ተደርገው እንደነበርም እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል። የምክር ቤት አባሉ ባለፈው እሁድ ወደ አሶሳ አየር ማረፊያ አቅንተው የነበረው፤ የፌደራል የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት እንደነበርም በወቅቱ አስረድተዋል።

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቶ ዮሐንስን ወደ አዲስ አበባ የጠራው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት ማሻሻያን በተመለከተ እርሳቸው እና ሌሎች ሁለት የቦዴፓ የክልል የምክር ቤት አባላት በጋራ በመሆን ያስገቡትን አቤቱታ በአካል ተገኝተው እንዲያስረዱ ነበር። ሆኖም የምክር ቤት አባሉ ካለፈው እሁድ ጀምሮ በአሶሳ ከተማ ወረዳ 2 ወደሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ በመታሰራቸው፤ በአጣሪ ጉባኤው የሚጠበቅባቸውን የማስረዳት ሂደት ሳያከናውኑ ቀርተዋል።
የምክር ቤት አባሉ በፖሊስ ጣቢያ ይታሰሩ እንጂ “ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ቃላቸውን መስጠት እንደማይፈልጉ” በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸውን የፓርቲው ምንጮች ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በ1995 ዓ.ም የወጣው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት “ማንኛውም የክልል ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፍቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።
በዚህም መሰረት ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ መደበኛ ጉባኤውን አካሄዶ የነበረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት፤ የአቶ ዮሐንስን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ለዛሬ አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቷል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የክልሉ ምክር ቤት አባላት፤ የዛሬውን አስቸኳይ ጉባኤ በተመለከተ ጥሪ የደረሳቸው በስልክ እንደሆነ እና የዕለቱ አጀንዳ ቀድሞ እንዳልተነገራቸው ገልጸዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤው የአቶ ዮሐንስን ያለመከሰስ መብት ከማንሳቱ አስቀድሞ፤ ይህንኑ በተመለከተ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሀሚድ የቀረበውን ማብራሪያ አድምጧል። አቶ መሐመድ በዚሁ ማብራሪያቸው ከየካቲት አጋማሹ መደበኛ ጉባኤ በኋላ፤ አቶ ዮሐንስ “የምክር ቤቱን ክብር የሚነኩና ሞገሱን ዝቅ የሚያደርጉ” እና “ግጭትን የሚቀሰቅሱ” መረጃዎችን “በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጭተዋል” ሲሉ ወንጅለዋል።
አቶ ዮሐንስ “ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና ለመነጠል የማነሳሳት ስራ መስራታቸውን፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨታቸውንና፣ መንግስትን በኃይል ለመናድ ከሚጥሩ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው” “አመላካች መረጃዎች” እንዳሉ የፍትህ ቢሮ ኃላፊው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። የምክር ቤት አባሉ ወንጀል ለመፈጸማቸው “በቂ የሆነ አመላካች ምክንያት በመታየቱና እና በወንጀል “በመጠርጠራቸው” ያለ መከሰስ መብታቸው ተነስቶ “በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ” ኃላፊው ለምክር ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል።
በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የተገኙ የምክር ቤት አባላት፤ አቶ ዮሐንስ “ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን” “በአመራር አካላት፣ ብሔር እና ግለሰቦችን” የተመለከቱ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲለቅቁ እንደነበር መናገራቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። በአቶ ዮሐንስ ሲሰራጩ የነበሩ መረጃዎች “ክልሉን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እና የሰላም እጦት የሚያስገባ በመሆኑ፤ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱ ተገቢ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ጽህፈቱ ቤቱ በመረጃው ላይ አስፍሯል።

የቀረበለትን ማብራሪያ እና የአባላትን አስተያየት ያደመጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት፤ የአቶ ዮሐንስን ያለመከሰስ መብት መነሳት “በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን” የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ካሉት 99 መቀመጫዎች 88ቱ የተያዙት በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው።
የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ስምንት ተወካዮች እና የቦዴፓ ሶስት ተመራጮች ቀሪዎቹን መቀመጫዎች ይዘዋል። በዛሬው የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ በእስር ላይ ከሚገኙት አቶ ዮሐንስ ውጪ ያሉት ሁለቱ የቦዴፓ የክልል ምክር ቤት አባላት አለመገኘታቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አቤቱታ የቀረበበት አዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት ማሻሻያ፤ የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫ አሁን ካለበት 99 ወደ 165 ከፍ አድርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]