የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በ13 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው   

በቤርሳቤህ ገብረ

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ በ13 አመት ጽኑ እስራት እና በ21 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የሀዋሳ ከተማ  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ። ፍርድ ቤቱ በእርሳቸው የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሌሎች አራት ተከሳሾች ላይም ከሶስት እስከ 10 ዓመት የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው ዛሬ አርብ መጋቢት 5፤ 2017 በዋለው ችሎት ነው። የሀዋሳ ከተማን ለሶስት ዓመታት የመሩት አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ “በህዝብ እና በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ” እንዲሁም “ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል” ወንጀል በፍርድ ቤቱ ክስ የቀረበባቸው በሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ነበር።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ በአቶ ጸጋዬ ላይ ክስ የመሰረተው፤ “በብልሹ አሰራር” እና “የአፈጻጸም ድክመት” ተገምግመው ከኃላፊነታቸው ከተነሱ ከአምስት ወራት በኋላ ነበር። የፍትህ ቢሮው በዚሁ ክሱ፤ ከሀይቅ ዳርቻ፣ ከታቦር ተራራ እና ከከተማይቱ ሚሊኒየም ፓርክ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ለተፈጸሙ “ያልተገቡ ክፍያዎች” እና “ከመመሪያ እና ደንብ ውጪ ለተከናወኑ ግዢዎች” አቶ ጸጋዬ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ወንጅሏል። 

በቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ላይ የቀረቡትን እነዚህን ክሶች ሲመረምር የቆየው የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በአቶ ጸጋዬ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ባለፈው ሳምንት አስተላልፎ ነበር። ፍርድ ቤቱ በዚሁ የችሎት ውሎ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት፤ የዐቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ እና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ አድምጧል።

አቶ ጸጋዬ ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች አንዱ በሆነው “በስልጣን አላግባብ መገልገል” የተጠቀሰባቸው አንቀጽ፤ ከሰባት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲሁም ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር በሆነ የገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ነው። የቀድሞው ከንቲባ በዚሁ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ መስረት የቀረበባቸው ሁለተኛም ክስም ተመሳሳይ የጽኑ እስራት ጊዜ እና ከሰባት ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር ቅጣት የያዘ ነው። 

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው፤ የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአቶ ጸጋዬ ላይ በድምሩ የ13 ዓመት ጽኑ እስራት እና የ21 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ በአቶ ጸጋዬ መዝገብ ሁለተኛውን ከፍተኛ የእስር ቅጣት ያስተላለፈው፤ የሀዋሳ ከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ በነበሩት አቶ ታሪኩ ታመነ ላይ ነው።

አቶ ታሪኩ በቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ ላይ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ ከተጠቀሱ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ “የመንግስት ስራን በማይመች አኳኋን በመምራት” ተወንጅለው ነበር። የቀድሞው ምክትል ኃላፊ፤ በሀዋሳ ከተማ ለሚገኙ ሀሰተኛ ሁለት የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በማዘጋጀትም በሲዳማ ክልል ዐቃቤ የሙስና ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

በሁለቱም ክሶች ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው አቶ ታሪኩ፤ በዛሬው የችሎት ውሎ  በ10 አመት ጽኑ እስራት እና በ41,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ እንደተሰጣቸው የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ እርሳቸው በኃላፊነት ይመሩት በነበረው መምሪያ ውስጥ ይሰሩ በነበሩ ሁለት መሀንዲሶች ላይም በዛሬው ዕለት በተመሳሳይ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል። 

“የመንግስት ስራ በማይመች አኳኋን መምራት” የሚል ክስ ከቀረበባቸው ከእነዚህ ሁለት ተከሳሾች ውስጥ አንደኛው የሆኑት አቶ ሰይፉ ደሊሳ፤ በስምንት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እና በ76 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉን የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ምንጮች ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ ታፈሰ ቱናሻ በተባሉት ሌላኛው ተከሳሽ ላይም የስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እና የ51 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት መጣሉን እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል። 

በቀደሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መዝገብ ከተካተቱ ተከሳሾች ዝቅተኛው ቅጣት የተፈረደባቸው፤ የአቶ ጸጋዬ ቱኬ ባለቤት አባት የሆኑት አቶ ተሰማ ዳንጉሼ ናቸው። አቶ ተሰማ የተከሰሱት፤ “ጉዳይ አስፈጽማላችኋለሁ” በማለት ከ11 የተለያዩ ማህበራት 150 ሺህ ብር በመሰብሰብ “የጉቦ ማቀባበል” ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ነበር። 

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህ ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ያገኛቸውን አቶ ተሰማን፤ በሶስት አመት ጽኑ እስራት እና በአንድ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ በዛሬው ዕለት መወሰኑን የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ በዚሁ የፍርድ ውሳኔው የአቶ ተሰማን የሶስት ዓመት ጽኑ እስራት በሁለት ዓመት እንዲገደብ ማድረጉንም ምንጮቹ አስረድተዋል።  

የገደብ ውሳኔው አቶ ተሰማ በሁለት ዓመት ውስጥ ወንጀል ካልፈጸሙ የቅጣት ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆንባቸው የሚያደርግ መሆኑን የቢሮው ምንጮች አስረድተዋል። አቶ ተሰማ ባለባቸው የጤና እክል ምክንያት፤ የዋስትና መብት ተሰጥቷቸው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው ሲከታተሉ መቆየታቸውንም አክለዋል።  

ከአቶ ተሰማ ጋር በጋብቻ የሚዛመዱት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ፤ በጥቅምት 2016 ዓ.ም. ከአሜሪካ ሲመለሱ በቦሌ አየር ማረፊያ በጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ ጀምሮ እስካሁንም በእስር እንዲቆዩ ተደርገዋል። አቶ ጸጋዬ ባለፈው የካቲት ወር በሌላ ፍርድ ቤት በቀረቡባቸው ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ ቢወስንላቸውም፤ በዛሬው ዕለት የጥፋተኝነት ውሳኔ በተላለፈባቸው ክሶች ምክንያት ከእስር ሳይለቀቁ ቀርተዋል። 

አቶ ጸጋዬን ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ነጻ ያደረጋቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው። በቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ላይ በዚህ ፍርድ ቤት ቀርቦባቸው የነበሩት ክሶች፤ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” እንዲሁም “በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስለው አቅርበዋል” የሚሉ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)