የትግራይ የጤና ባለሙያዎች የ17 ወራት ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በሰልፍ ጠየቁ

የትግራይ ክልል የጤና ባለሙያዎች በክልሉ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ሳያገኙ የቀሩት የ17 ወራት ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በሰልፍ ጠየቁ። የጤና ባለሙያዎቹ ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል። 

ባለሙያዎቹ ጥያቄያቸውን ያሰሙት፤ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 29፤ 2017 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት ውስጥ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ነው። ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት እንደሚካሄድ የተገለጸውን ይህ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው የትግራይ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ነው። 

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍስሃ አሸብር የጤና ባለሙያዎች በትግራይ ጦርነት ወቅት በስራ ገበታቸው በመገኘት ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የጤና ባለሙያዎቹ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት፤ ለ17 ወራት ያህል ደመወዝ ሳይከፈላቸው እንደነበርም ጠቁመዋል።

ባለሙያዎቹ የዛሬውን ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱት፤ ውዝፍ ደመወዛቸው እና በጊዜው በትርፍ ሰዓት ያገለገሉበት ክፍያ እንዲከፈላቸው መሆኑን ዶ/ር ፍስሃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጤና ባለሙያዎች በዚሁ ሰልፋቸው የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው፣ ከደመወዛቸው የሚቆረጥ ግብር እንዲቀንስላቸው፣ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጣቸው እና የመኖሪያ ቤት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

በሰልፉ ላይ የጤና ባለሙያዎች በችግርነት ከጠቀሷቸው ጉዳዮች ውስጥ የትራንስፖርት አቅርቦት አለመዘጋጀት እና በጤና ተቋማት የህጻናት ማቆያ አለመኖር ይገኙበታል። የትግራይ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ባለፈው ዓመት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በጋራ ባደረገው ጥናት መሰረት፤ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት 921 የጤና ባለሙያዎች ክልሉን ለቅቀው እንዲወጡ ተገድደዋል። 

በተመሳሳይ ምክንያት ብዛት ያላቸው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም “የስራ ዘርፍ እንደቀየሩ” ማህበሩ አስታውቋል። በዛሬው የመቐለ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች፤ ጥያቄያቸው ሰላማዊ መሆኑን ለማሳየት በግራ እጃቸው ጥቁር ጨርቅ አስረው ታይተዋል። ከመቐለ በተጨማሪ በውቅሮ፣ አድዋ፣ ሞኾኒ እና ሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ሰልፉ መካሄዱንም ለማወቅ ተችሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)