የኢቢኤስ ቴሌቪዥን እና ሶስት የጣቢያው ሰራተኞች በጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተከሰሱ 

በተስፋለም ወልደየስ

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን፣ እህት ኩባንያው እና ሶስት የጣቢያው ሰራተኞች የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ክስ ቀረበባቸው። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረበው በዚህ የክስ መዝገብ ክስ፤ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ፣ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን “ሀሰተኛ ታሪኳ ተሰራጭቷል” የተባለችው ብርቱካን ተመስገንን ጨምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎች በሽብር ወንጀል ተከስሰዋል።

በአጠቃላይ 16 ተከሳሾች የተካተቱበትን የክስ መዝገብ፤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህገ መንግስት እና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 28፤ 2017 ያቀረበው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ነው። ከተከሳሾቹ መካከል ስምንቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቢሮ እና በወረዳ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ናቸው። 

ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው መዝገብ ሶስት የክስ አይነቶች ጠቅሷል። የመጀመሪያው ክስ፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በ2011 ዓ.ም. የወጣን አዋጅ በመተላለፍ የቀረበ ነው። ዐቃቤ ህግ በክሱ የጠቀሰው የአዋጁ ድንጋጌ፤ “የሽብር ድርጊት” በመፈጸም “የሰው ህይወትን ለአደጋ ማጋለጥን” ይመለከታል። 

ማንኛውም ሰው “የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ፣ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ ሀገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ” የሽብር ድርጊቱን የሚፈጽም ከሆነ፤ ከ10 ዓመት እስከ 18 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚቀጣም በአዋጁ ተደንግጓል። ይህ ድንጋጌ ተጠቅሶ ክስ ከቀረበባቸው ተጠርጣሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት የተቀመጡት በአሁኑ ወቅት ነዋሪነታቸውን በውጭ ሃገር ያደረጉት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ተስፋዬ ወልደስላሴ ናቸው። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 14፤ የሲቪል ምዝገባ እና ነዋሪዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሳሁን ኃይሌ እና በዚሁ ወረዳ የስራ ስምሪት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዋለልኝ አለማየሁ በመጀመሪያው ክስ የተካተቱ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ናቸው። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 የጤና መድን ባለሙያ የሆኑት አቶ ልጅ አዲስ አጥናፉም እንዲሁ በተመሳሳይ ድንጋጌ ተከስሰዋል።

ለክሱ መቅረብ ምክንያት የሆነችው እና “አዲስ ምዕራፍ” በተሰኘው የኢቢኤስ ፕሮግራም “ሀሰተኛ ታሪኳ” ተሰራጭቷል የተባለችው ብርቱካን ተመስገንም፤ እንደ አምስቱ ተከሳሶች ሁሉ የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባታል። ብርቱካን ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤት ባቀረበው መዝገብ በሶስተኛነት ባሰፈረው ክስ ላይም ተካትታለች። 

የዐቃቤ ህግ ሶስተኛ ክስ፤ በ2007 ዓ. የወጣውን የሙስና ወንጀሎች አዋጅን በመተላለፍ የቀረበ ነው። በዚህ ክስ የተጠቀሰው የአዋጁ ድንጋጌ “በስልጣን አላግባብ መገልገልን” የሚመለከት ሲሆን፤ ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ10 ሺህ ብር እስከ 100 ሺህ ብር በሚሆን የገንዘብ ቅጣት የያዘ ነው።

ይህ ቅጣት ተፈጻሚ የሚሆነው “ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ፤ በግለሰብ፣ በመንግስት ወይም በህዝባዊ ድርጅት ጥቅም ወይም በህዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የተፈጸመውን ወንጀል ከባድ ካደረገው እንደሆነ” በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። ይህ ክስ ከቀረበባቸው ሰባት ተከሳሾች መካከል ስድስቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች ናቸው።

የኢቤኢስ ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ሰራተኞቹን በሚመለከተው ሌላኛው የዐቃቤ ህግ ክስ ደግሞ አምስት ተከሳሾች ተዘርዝረዋል። በ2012 ዓ.ም የወጣውን የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ ሁለቱ ድርጅቶች ናቸው። 

በዚሁ አዋጅ መሰረት ክስ የቀረበበት የመጀመሪያው ድርጅት ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ኃ.የተ.የግ.ማ ሲሆን ሌላኛው የጣቢያው እህት ኩባንያ የሆነው ሲልቨር ስፕሪንግ ፕሮዳክሽን እና ፕሮሞሽን ኃ.የተ.የግ.ማ ነው። የእህት ኩባንያ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ማክዳ አሰፋ በዚህ ክስ ስር ተካትተዋል። የኢቢኤስ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ማክዳ በአሁኑ ወቅት “በውጭ ሃገር በመሆናቸው” በዛሬው ዕለት በአካል ችሎት ፊት አልቀረቡም።

የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ሌሎች የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ሰራተኞች አቶ ታሪኩ ኃይሌ እና ህሊና ታቀረኝ ናቸው። ታሪኩ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን “አዲስ ምዕራፍ” ፕሮግራም ዳይሬክተር ሲሆን ህሊና የዚሁ ፕሮግራም አዘጋጅ እና ረዳት ዳይሬክተር ነች። 

ሁለቱ ድርጅቶች እና ሶስት የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች ክስ የቀረበባቸው፤ በ2012ቱ አዋጅ “የጥላቻ ንግግር” እና “የሐሰተኛ መረጃን ማሰራጨት” ስለመከልከሉ የሰፈሩ ድንጋጌዎች በመተላለፍ ነው። በዚሁ አዋጅ “የወንጀል ተጠያቂነትን” የተመለከተው አንቀጽም በተከሳሾቹ ላይ ተጠቅሶባቸዋል። 

ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ የጠቀሰው ይህ አንቀጽ “የጥላቻ ንግግር ወይም የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከ100 ሺህ ያልበለጠ ይሆናል” ሲል ይደነግጋል።

ዛሬ ከሰዓት በተካሄደው የችሎት ውሎ፤ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ለተከሳሾች እና ለጠበቆች እንዲደርስ ተደርጓል። የችሎቱ የመሃል ዳኛ የክሱን ዝርዝር በንባብ ካቀረቡ በኋላ ከአንድ ተጠርጣሪ በስተቀር ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። እስከ ሚቀጥለው ቀጠሮ ድረስ አሁን በሚገኙበት የፌደራል ፖሊስ የእስረኞች ማቆያ እንዲቆዩ ትዕዛዝ የተላለፈላቸው፤ በክስ ዝርዝሩ በ13ኛ ደረጃ ላይ የሰፈሩት ወ/ሮ ዘሃራ ከድር ናቸው። 

ጨቅላ ህጻን ልጃቸውን ታቅፈው ችሎት ፊት የቀረቡት ዘሃራ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 14 የሴቶች እና ህጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። የአራት ህጻናት ልጆች እናት መሆናቸውን የጠቀሱት ዘሃራ፤ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። 

ፍርድ ቤቱ በዛሬው የችሎት ውሎ የተከሳሾችን የመብት ጥያቄዎች እንደማይስተናገድ የገለጹት ዋናው ዳኛ፤ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ለማድመጥ ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 5፤ 2017 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱ በመጪው ቀጠሮው፤ በአካል ያልቀረቡ ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥም ዳኛው አስታውቀዋል።

የከሰዓቱ ችሎት ከመካሄዱ አስቀድሞ ረፋዱን የተሰየመው የፌደራል ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ አራት የኢቤኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች ዋስትና በማስያዝ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ከእነዚህ ሰራተኞች መካከል የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ጥዑመልሳን ይገኙበታል። አቶ ነብዩ ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው በ30 ሺህ ብር ዋስትና ነው።

በተመሳሳይ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የስቱዲዩ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ንጥር ደረጀ፣ የኤዲቲንግ ሱፐርቫይዘሩ አቶ ሄኖክ አባተ እና ኤዲተሩ አቶ ሀብታሙ አለማየሁ እያንዳንዳቸው 20 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ እንዲለቀቁ ችሎቱ በረፋድ ውሎው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ይህን ተከትሎ የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች በፍርድ ቤት የተጠየቀውን ዋስትና ክፍያ ቢፈጽሙም፤ አራቱም የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሳይፈቱ መቅረታቸውን በስፍራው የነበሩ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)