አቶ ጌታቸው ረዳ ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ሰራዊት አመራሮች “በዘረፋ እና በሰዎች ንግድ ላይ ተሳትፈዋል” ሲሉ ወነጀሉ   

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች “በወርቅ ቁፋሮ እና ንግድ”፣ “የመንግስት ገንዘብ በመዝረፍ” እንዲሁም ”በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል” ሲሉ ወነጀሉ። አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በስም ጠቅሰው የወነጀሏቸው ሶስቱ አመራሮች፤ ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሃይለ፣ ብርጋዴር ጀነራል ሃይለስላሴ ግርማይ እና ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ ናቸው። 

ትላንት ሰኞ ግንቦት 4፤ 2017 ምሽት በፋና ቴሌቪዥን በተላለፈው የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ክፍል አንድ ቃለ መጠይቅ፤ ስለ እርሳቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አጀማመር፣ በትግራይ ክልል ስለ ተካሄደው ጦርነት፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች እና የትግራይ ሰራዊት አዛዦች “ፈጽመዋቸዋል” ስላሏቸው ወንጀሎች የዘረዘሩበት ነበር። አቶ ጌታቸው ተፈጽመዋል ካሏቸው ወንጀሎች ቅድሚያውን የሰጡት ለወርቅ ንግድ ነው።

በትግራይ ክልል በህገወጥ መንገድ የሚካሄደው የወርቅ ንግድ የተጀመረው፤ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያ ስምምነትን ከተፈራረሙ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. በኋላ የሚመስለው በርካታ ሰው እንዳለ አቶ ጌታቸው በቃለ መጠይቃቸው ላይ አንስተዋል። ሆኖም በክልሉ ህገወጥ የወርቅ ቁፋሮም ሆነ ንግድ የተጀመረው፤ የትግራይ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ጭምር እንደሆነ የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ይፋ አድርገዋል።    

ፎቶ፦ ከፋና ቴሌቪዥን ቃለ መጠየቅ የተወሰደ

“ጦርነት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እኔ የማምንበት resistance ነው ያካሄድኩት። የማምንበት ትግል ነው ያካሄድኩት ብዬ ነው የማምነው። በዚያ በማምንበት ትግል ውስጥ የትግራይን አጀንዳ ይዘው የታገሉ፣ ብዙ የጦር መኮንኖች አሉ። ለሰሩት ስራ ያለኝ ክብር በፍጹም ሊቀንስ አይችልም። ግን ደግሞ ጦርነቱ ገና በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ይበላ በነበረበት ወቅት ሳይቀር፤ ምሽግ ለመቆፈር ብለን የወሰድነውን ኤክስካቫተር ወርቅ ለመልቀም ይጠቀሙበት የነበሩ አዛዦችም አሉ” ሲሉ አቶ ጌታቸው ከስሰዋል።

አቶ ጌታቸው “በወርቅ ንግድ ላይ ተሰማርተዋል” በሚል በስም የጠቀሷቸው የጦር መኮንን ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሃይለን ነው። ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ፤ አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነታቸውን ከማስረከባቸው አንድ ወር ገደማ በፊት ከስራ ካገዷቸው ሶስት የጦር አዛዦች አንዱ ናቸው። 

“ዳባት፣ ደባርቅ አካባቢ ሊማሊሞ ውጊያ ይመራ የነበረ ሰው፣ ሩቅ ርቀት ሆኖ ውጊያ ይመራ የነበረ ሰው፤ በተመሳሳይ ጊዜ በኤክስካቫተር ወርቅ እየቆፈረ ይሸጥ ነበረ” ሲሉ አቶ ጌታቸው ወንጅለዋል። “ወርቅ ንግድ ውስጥ የገባ፤ ‘ለትግራይ ነጻነት አሁንም እስከመጨረሻው እሰዋለሁ’ እያለ የሚፎክር ጄነራል አለ። ወርቅ ንግድ [ውስጥ] ነው ያለኸው መባል አለበት” ሲሉ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ የጦር መኮንኖች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።   

ፎቶ፦ ከወይን ዩቲዮብ ቻናል የተወሰደ

“እነ ምግበይ ይሰሩት ጀግንነት የወጣት መስዋዕትነት መሰረት ተደርጎ የመጣ ጀግንነት ነው። እነዚያን ወጣቶች ለስደት በሚዳርግ ደረጃ ወደ ተራ የወርቅ ንግድ ገብተው ሲያበቁ፤ የስርቆት ተግባራቸውን የትግራይ ግዛት አንድነት የማረጋገጥ አድርገው፤ እንደገና ለሌላ መስዋዕትነት ይሄን ወጣት ሊዳርጉ [እየተንቀሳቀሱ ነው]” ሲሉም አቶ ጌታቸው ከስሰዋል። ይህ እንቅስቃሴ “በትግራይ ወጣት መስዋዕትነት እንድናለን የሚል አስተሳሰብ የወለደው ነው” ብለዋል። 

አቶ ጌታቸው በዚሁ ቃለመጠይቃቸው በስም የጠቀስዋቸው ሌላኛው ወታደራዊ አመራር ብርጋዴር ጄነራል ሃይለስላሴ ግርማይ (ወዲ እምበይተይ) ናቸው። ብርጋዴር ጄነራል ሃይለስላሴ በ2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ኮምቦልቻን በተቆጣጠሩበት ወቅት በመንግስት ባንኮች ውስጥ የነበረውን ገንዘብ እንዲሰበስቡ ከተመደቡ ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ አቶ ጌታቸው አስታውሰዋል።

በወቅቱ በመንግስት ባንኮች የነበረው አራት ቢልዮን ብር እንደነበር የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ብርጋዴር ጄነራል ሃይለስላሴ “አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ ነው የወሰደው” ሲሉ ከስሰዋል። በወቅቱ የግንባር አዛዥ ከነበሩት ብርጋዴር ጄነራል ሃይለስላሴ ስር የነበሩ ሌሎች ሰዎችም፤ “የተወሰነ ድርሻ መውሰዳቸውንም” አቶ ጌታቸው አክለዋል።

ፎቶ፦ ከወይን ዩቲዮብ ቻናል የተወሰደ

እነ ብርጋዴር ጄነራል ሃይለስላሴ የወርቅ መቆፈሪያ ማሽን ከውጭ ሀገር በማስገባት፤ በፌደራል መንግስት ሲያዝባቸው ለማስለቀቅ ሙከራ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጨምረው ገልጸዋል። “እነ ምግበይ፣ እነ ኃይለስላሴ በወንጀል ተነክረው፤ ድንገት የሆነ ሰላም ከተፈጠረ ‘አደጋ ውስጥ እገባለሁ፣ ተጠያቂ እሆናለሁ’ ብለው የሚያስቡ ሰዎች፤ ግርግር በፍጹም እንዲያልቅ አይፈልጉም” ሲሉም አቶ ጌታቸው ነቅፈዋል።

በትግራይ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው አቶ ጌታቸው፤ የትግራይ ሰራዊት የመረጃ መምሪያ ኃላፊ የነበሩትን ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤንም (ዕምበብ) በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በነበራቸው ሚና ተጠያቂ አድርገዋቸዋል። በቅርቡ ከሃገር እንደወጡ የተነገረላቸው ኮሎኔል ተወልደ፤ ኤርትራውያንን “እንደ ንብረት ይሸጡ” ከነበሩ ሰዎች አንዱ እንደነበሩ አቶ ጌታቸው በቃለ መጠይቃቸው ላይ ጠቅሰዋል። 

በትግራይ በኩል የነበረው ዓላማ የኤርትራን ሰራዊት ለማፍረስ “ሰዎች እንዲመጡ ማድረግ” የሚል እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ይህ ዘመቻ በስተኋላ ላይ ገንዘብ ያላቸውን ኤርትራውያንን ወደ “ማፈን”፣ “ማገት” እና “መሸጥ” መቀየሩን አስረድተዋል። ኤርትራውያን ወጣቶች ከተያዙ በኋላ በውጭ ሀገራት ቤተሰቦች ያሏቸውን በመለየት፤ እያንዳንዱ ሰው “በትንሹ አራት ሺህ ዶላር እንዲያስገባ ይደረግ” እንደነበር አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

ፎቶ፦ ከብራኸ ሾው ዩቲዮብ ቻናል የተወሰደ

ይህን አካሄድ በመጠቀም “የውጭ አካውንት ከፍተው”፣ “በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያገቱ” ኤርትራውያንን “የሚሸጡ” የትግራይ ሰራዊት አመራሮች እንደነበሩ በጦርነቱ ወቅት የሴንትራል ኮማንድ አባል የነበሩት አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። ይህ በኤርትራውያን ላይ ሲካሄድ የቆየው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፤ “በስተመጨረሻ ወደ ትግራይ ተወላጆችም መዞሩንም” አመልክተዋል።

የሰዎች ዝውውር ንግዱ ተጧጡፎ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ሰዎች አሁንም እንዳሉ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ በዚህ አካሄድ “የኤርትራ ሰራዊትን ማፍረስ አይቻልም” ብለዋል። “ምክንያቱም ገንዘብ ያለው ሰው ነው ሊወጣ የሚችለው። ወጣቶች መዋጋት የማይፈልጉ ግን ደግሞ ታፍነው፣ ገንዘብ አውርዱ እንዳይባሉ፣ ስቃይ ውስጥ እንዲቀጥሉ የተደረጉ አሉ” ሲሉ ሁኔታውን አስከፊነት አስረድተዋል።

አቶ ጌታቸው በትግራይ ወታደራዊ አመራሮች ተፈጽመዋል ካሏቸው ወንጀሎች ጀርባ “የፖለቲካዊ አመራሩ እጅ አለበት” ሲሉም ከስሰዋል። ከእነዚህ ወንጀሎች ጋር የተያያዙ መረጃዎች፤ እርሳቸው የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት መሰብሰቡን እና የተደራጀ ሰነድ እንዳለም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል። ይህ ሰነድ ለክልሉ ፍትህ ቢሮ፣ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እና ፖሊስ ኮሚሽን እንደቀረበም አክለዋል።

“ይሄንን ለማስፈጸም ኃላፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች የእኔ ሰዎች ናቸው። የጸጥታ አመራሮች ናቸው። የጸጥታ አመራር በባህሪው፤ ጥፋት ያጠፋውም፣ ያላጠፋውም የመተጋገዝ ባህሪ አለው”

– አቶ ጌታቸው ረዳ

በወንጀል ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች እርምጃ ሳይወሰድባቸው የቀረው፤ በጸጥታ አመራሮቹ እምቢተኝነት መሆኑንም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። “ይሄንን ለማስፈጸም ኃላፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች የእኔ ሰዎች ናቸው። የጸጥታ አመራሮች ናቸው። የጸጥታ አመራር በባህሪው፤ ጥፋት ያጠፋውም፣ ያላጠፋውም የመተጋገዝ ባህሪ አለው” ሲሉ የህግ ማስከበር እርምጃው እስካሁን ተግባራዊ ያልተደረገበትን ምክንያት አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)