ለጤናው ዘርፍ በ2018 ዓ.ም. “ከፍ ያለ” በጀት ለመመደብ፤ “በቂ ዝግጅቶች” እየተደረጉ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናገሩ። የዘርፉን በጀት ከፍ ማድረግ ያስፈለገው አሁን ካለው “ወቅታዊ” እና “ነባራዊ” ሁኔታ አንጻር እንደሆነም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ይህን ያሉት ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት እና ዛሬ ሰኞ ግንቦት 4፤ 2017 በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው ነው። ዶ/ር በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው፤ የጤና ዘርፉን በተመለከተ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሚኒስትሯ ካቀረበው ጥያቄ አንዱ፤ የጤናው ዘርፍ የገንዘብ አቅምን የተመለከተ ነው። መንግስት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ ለጋሾች በሚሰጡት ገንዘብ በሚደገፈው በዚህ ዘርፍ፤ በአሁኑ ወቅት ስራዎች በምን መልኩ እየተሰሩ እንደሆነ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ ለሚኒስትሯ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ዶ/ር መቅደስ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ የሚመደበው በጀት ባለፉት ዓመታት እየጨመረ ቢመጣም፤ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንጻር ሲታይ መጠኑ “ዝቅተኛ” መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትሯ ለዚህ በማጣቀሻነት ያነሱት፤ በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) የመሪዎች ጉባኤ ላይ በሚያዝያ 1993 ዓ.ም. የጸደቀውን የአቡጃ ድንጋጌ ነው።
በናይጄሪያ አቡጃ ከተማ በተካሄደው በዚህ የመሪዎች ጉባኤ፤ የድርጅቱ አባል ሀገራት ከዓመታዊ በጀታቸው 15 በመቶውን ያህል የጤና ዘርፉን ለማሻሻል ለመመደብ ቃል የገቡበት ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ለ2016 በጀት ዓመት በፓርላማ ካጸደቀው 801.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ፤ የጤናው ዘርፍ የነበረው ድርሻ 3.93 በመቶ ነበር።
በዚሁ በጀት ዓመት ዘርፉ ከፌደራል መንግስት የመደበኛ እና የካፒታል ወጪ ያገኘው ገንዘብ፤ ከዕዳ ክፍያ፣ ከመንገድ፣ ከትምህርት እና ከመከላከያ በመከተል በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። የጤናው ዘርፍ በፌደራል መንግስት የ2017 በጀትም፤ በተመደበለት ገንዘብ መጠን ሲታይ በተመሳሳይ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

ለዘርፉ በ2016 በጀት ዓመት የተመደበው 22.57 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ ይህ መጠን በተያዘው በጀት ዓመት ወደ 33.90 ቢሊዮን ብር አድጓል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ያጸደቀው በጀት መጠን 971.2 ቢሊዮን ብር ነበር። ለጤናው ዘርፍ የሚመደበው በጀት ከዓመት ወደ ዓመት “ጨመር እያለ” መምጣቱን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልሳቸው የጠቀሱት ዶ/ር መቅደስ፤ “ያ ግን በቂ አይደለም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
መስሪያ ቤታቸው ዘርፉ ለ2018 የሚያስፈልገውን በጀት በአሁኑ ወቅት “እየሰራ” መሆኑን የጠቆሙት የጤና ሚኒስትሯ፤ አሁን ካለው “ወቅታዊ” እና “ነባራዊ ሁኔታ” አንጻር በምን መልክ “ከፍ ያለ በጀት” ማዘጋጀት እንደሚቻል እየታየ መሆኑን አስረድተዋል። “ቀደም ብለን በጣም ብዙ ነገሮችን እያየን [ነው]። ‘በምን ቦታ ላይ ክፍተት ይመጣል? በግብዓት ቦታ ላይ ነው? የቱ ጋር ነበር ድጋፎች የምናገኘው? የትኞቹ ድጋፎች ይቀጥላሉ? የትኞቹን ደግሞ በዘላቂነት ፈትተን መሄድ የምንችልበትን ስራ ትኩረት ሰጥተን [እየሰራን] ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
“የትኛውም አይነት አጋር ድርጅቶች እና ለጋሽ ድርጅቶች በሚያመጡት ላይ አዲስ በጀት ጨምረን በመምጣት፤ በእርግጠኝነት በዚህኛው ዓመት ከፍ ያለ በጀት መድቦ ለዘርፉ ማሰራት የሚቻልበትን…ለዚያ ብዙ፣ በቂ ዝግጅቶች እያደረግን ነው” ብለዋል ሚኒስትሯ። ይህ ሂደት ከፍተኛ “ትግስት፣ አብሮ መስራት፣ ቆጣቢነት እና ፈጣሪነት ይፈልጋል” ሲሉም ተደምጠዋል።
“ጊዜ የሚፈልጉ፣ እስክንሻገራቸው እና እስክናልፋቸው ድረስ ተባብረን መስራት ያለብን [ጉዳዮች አሉ]” ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ በዘርፉ ላይ የሚታየውን የበጀት ክፍተት በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡን ጨምሮ ሁሉም አካላት “ተረባርበው” መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የፌደራል መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት “ቁርጠኝነት” እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ረገድ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ለዚህም በማሳያነት የጠቀሱት፤ ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ለሚሰጡት ገንዘብ የፌደራል መንግስትም እኩል መጠን ያለው በጀት ከራሱ በmatching fund አሰራር አብሮ መመደብ መጀመሩን ነው። ይህ አሰራር ባለፉት ሶስት ዓመታት እየተተገበረ መቆየቱን ያመለከቱት ዶ/ር መቅደስ፤ “የሚመጡ በጀቶችን የማሻሻል” እና ገንዘብ አብሮ የመመደብ አካሄድ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































