የትግራይ ክልል “ወደ ጦርነት እንዳይገባ” የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን እና ኤምባሲዎች ሚናቸውን “በፍጥነት” እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። በትግራይ ውጊያ ከተጀመረ፤ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 26፤ 2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። በሁለት ክፍል የቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቅድሚያውን እና ሰፊውን ጊዜ የሰጠው፤ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ለቀረቡ ጥያቄዎች ነበር።
ሶስት ሰዓት ገደማ ከፈጀው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ውስጥ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ የተመደበለት አንድ ሰዓት ያልሞላ ጊዜ ነበር። በዚህኛው የማብራሪያ ክፍል ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ ትግራይ እና ኤርትራን የተመለከቱት ይገኙበታል።

“የትግራይ ህዝብ መቶ ፐርሰንት ጦርነት አይፈልግም” ያሉት አብይ፤ ከህዝብ ፍላጎት እና አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ በክልሉ ውጊያ ቢቀሰቀስ “ዓለም ደንታ የለውም” ብለዋል። “[ዓለም] ብዙ ውጊያ እያስተናገደ ስለሆነ፤ ጆሮም የለውም፣ ጊዜም የለውም። ዓለም ጊዜ ቢኖረው ኖሮ ሱዳንን ያዳምጥ ነበር” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።
አብይ በማብራሪያቸው “አንዳንዶች” ሲሉ የገለጿቸው ግለሰቦች፤ “የሚያግዙን ሰዎች እና ሃገራት አሉ” ብለው እንደሚያስቡ ጠቅሰዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ “ትላልቅ ውጊያዎች” እንኳን “መደጋገፍ ችግር ሆኗል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ከራስ ተርፎ ሰው ለማገዝ የማያስችል” ሆኗል ያሉት የዓለም ኢኮኖሚ እንደሆነ አስረድተዋል።
“እነዚህ ሀገራት እንኳን እናንተን እራሳቸውን ማገዝ አይችሉም። ሞራል ቲፎዞነት እና ማገዝ ለየብቻ ነው፤ ስታዲየም ተቀምጦ ማጨብጨብ እና ኳስ ሜዳ ገብቶ መጫወት ለየብቻ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከሌሎች ሀገራት “እገዛ እናገኛለን” ብለው ማሰብ “ስሁት ግምገማ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
“እነዚህ ሀገራት እንኳን እናንተን እራሳቸውን ማገዝ አይችሉም። ሞራል ቲፎዞነት እና ማገዝ ለየብቻ ነው፤ ስታዲየም ተቀምጦ ማጨብጨብ እና ኳስ ሜዳ ገብቶ መጫወት ለየብቻ ነው”
– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
በእነዚህ ግለሰቦች ዘንድ “የአለምን ነገር” እና “የዘመኑን የውጊያ ስልት” “አለመገንዘብ” እንደሚስተዋል የተናገሩት አብይ፤ “እንደ ድሮው ተራራ መያዝ፣ ተራራ መልቀቅ ብቻ ማሰብ” ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል። ለዚህ በቅርቡ በኢራን እና በእስራኤል መካከል የተካሄደውን ጦርነት በማሳያነት አንስተዋል። “ኢራንን እና እስራኤልን ያዋጋው ተራራ አይደለም፤ ዘመን ተቀይሯል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“መንግስት በሸኔ እና በፋኖ ተወጥሯል” የሚል አመለካከት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ደግሞ፤ “መንግስት ወታደር ስለተበታተነበት። ጊዜው አሁን ነው” እንደሚሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። “እነዚህ ሰዎች ታሪክ መለስ ብለው ማየት በቂያቸው ነው” ያሉት አብይ፤ ይህንኑ ለማስረዳት የጣሊያን እና ሶማሊያን ወረራዎች አስታውሰዋል።
“ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር፤ እንኳን የተበተነ – ወታደር አልነበረንም። ጣልያን ኢትዮጵያን ስትወር ወታደር አልነበረንም፤ ከበሮ ነው የነበረን። ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል የግድ ሰልፍ የያዘ ወታደር አያስፈልጋትም። ታሪኳ እሱን አያሳይም። እኛ የተሻለ አቅም አለን ግን ያም ቢሆን፣ ሌሎቹም ቢሆን በዚያ መሰላት የለበትም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የትግራይን ጉዳይ “በሰላም እና በውይይት መፍታት ይቻላል” ያሉት አብይ፤ በትግራይ እና በኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም በክልሉ ባሉ ኃይሎች ዘንድ “ጦርነት አያስፈልግም” የሚለው “መታወቅ ያለበት” ጉዳይ እንደሆነ አሳስበዋል። የትግራይ ክልል በድጋሚ “ወደ ጦርነት እንዳይገባ” ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
“የሃይማኖት አባቶች፣ የሁሉም እምነት አባቶች እዚህ ተወካዮች አላችሁ። ሌላ ምንም ስራ የላችሁም። ትግራይ ወደ ግጭት እንዳይገባ፣ ወደ ጦርነት እንዳይገባ፤ ስራችሁን በፍጥነት አሁን ጀምሩ። ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬ ስብሰባ ላይ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል። ባለሀብቶች፣ ምሁራን እና ኤምባሲዎችም በየበኩላቸው “ውጊያ እንዳይጀመር” የሚያስችላቸውን ስራ እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል።
“[ውጊያ] ከተጀመረ፤ ከዚህ በፊት የምናውቀው [አይነት] አይደለም። ነገር ይበላሻል። አሁን ሚናችሁን ተወጡ። በእኛ በኩል በትግራይ ምድር አንድ ጥይት መተኮስ ፍላጎት የለንም፤ ከቻልን ማልማት ነው የምንፈልገው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]
































