በሽፋን ምርመራ ወቅት “ከግድያ በስተቀር” የሚፈጸም ወንጀልን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው አወዛጋቢ ድንጋጌ ተሰረዘ

በቤርሳቤህ ገብረ

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን “በሽፋን ስር” ሆኖ የመመርመር ኃላፊነት የተሰጠው ሰው፤ “ከግድያ በስተቀር” የሚፈጽማቸውን የወንጀል ድርጊቶች ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው ድንጋጌ ተሰረዘ። ድንጋጌው የተሰረዘው አዋጁ “በሰፊው እንዲተረጎም ስለሚያደርግ” እና በአተገባበሩም ላይ “አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስከትል ስለሆነ ነው” ተብሏል። 

አወዛጋቢው ድንጋጌ ተካትቶ የነበረው፤ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ላይ ነበር። እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከ12 ዓመት በፊት የወጣውን ህግ ያሻሻለው አዲሱ አዋጅ በፓርላማ የጸደቀው ሰኔ 10፤ 2017 ዓ.ም. ነበር።

በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራን በተመለከተ በዚህ አዋጅ ላይ የተካተተ ድንጋጌ፤ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትችት ቀስቅሶ ሰንብቷል። ድንጋጌው “በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው፤ በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም” ይላል።

“በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው፤ በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም”

– ከአዋጁ ላይ እንዲሰረዝ የተደረገው ድንጋጌ

አዋጁ በጸደቀበት ዕለት የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማ አባላት ያቀረበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚቴ፤ ድንጋጌው እንዲካተት የተደረገው “ልዩ የምርመራ ስራን” “ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ገልጾ ነበር። ቋሚ ኮሚቴው “ልዩ የምርመራ ዘዴን” በመጠቀም ስራውን የሚያከናውን ሰው፤ “የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰራ መሆኑን” እንደ ደጋፊ ምክንያት ማቅረቡም ይታወሳል።

ይሁንና ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 30 በተደረገ የተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ፤ ድንጋጌው እንዲሰረዝ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። ድንጋጌው “አዋጁ በሰፊው እንዲተረጎም የሚያደርግ እና አተገባበሩ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስከትል ስለሆነ፤ አዋጁ ለህትመት ያልበቃ እና በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ፤ ቀሪ እንዲሆን ይህ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኢሳ ቦሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

በዚህ የውሳኔ ሃሳብ ላይ አራት የፓርላማ አባላት አስተያየት ሰጥተዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ የሆኑት ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ አቶ ባርጠማ ፈቃዱ፤ አዋጁ ተመልሶ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምጣቱን “የምክር ቤቱ አቅም ጭምር የሚያሳይ ነው” ሲሉ አድነቀዋል። አዋጁ ተመልሶ ወደ ፓርላማው መምጣቱ ሲሉ አሞካሽተውታል።

እንደ አቶ ባርጠማ ሁሉ ሌሎች ሁለት የፓርላማ አባላትም በአዋጁ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ደግፈዋል። አዋጁ በሚጸድቅበት ወቅት ድንጋጌውን “ትክክል ነው” ብለው ሲከራከሩ የነበሩ የፓርላማ አባላት እንደነበሩ ያስታወሱት የኢዜማው ተወካይ፤ በዛሬው ልዩ ስብሰባ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መደገፋቸው “በአንድ ምላስ ሁለት እራስ ያስብላል” ሲሉ ተችተዋል።

የውሳኔ ሀሳቡ በአንድ ድምጽ ተዐቅቦ ከመጽደቁ አስቀድሞ የመናገር እድል ያገኙ ሌላ የፓርላማ አባል፤ አዋጁ በሚጸድቅበት ጊዜ በድንጋጌው ላይ “በመሰረታዊነት ክርክር” መደረጉን አንስተዋል። በድንጋጌው ላይ “የተለያየ መልክ” ያለው “ጫጫታ” በብዛት ሲሰማ እንደነበር የፓርላማ አባሉ አክለዋል።

አዋጁ በጸደቀበት ወቅት “በምርመራ ወቅት የሚመረምረው አካል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ጊዜ፤ ከዚህ ውጪ ሊያደርግ የሚችለው ጉዳይ እንደሌለ፣ ዋስትና ሊያገኝ እንደሚገባ በደንብ ማብራሪያ የተሰጠበት ጉዳይ ነበር” ሲሉ እኚሁ የፓርላማ አባል አስታውሰዋል። ድንጋጌው ከአዋጁ ውስጥ እንዲወጣ ሲደረግ፤ መርማሪዎች የተሰጣቸውን ዋስትና የሚያስቀር በመሆኑ ቀድሞ የጸደቀው ባለበት ቢቀጥል እንደሚሻል ተናግረዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“የሚመረምሩ ሰዎች፣ አደገኛ ችግር ውስጥ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ፤ የእዚህ አይነት ዋስትና ሊያገኙ የማይችሉ ካልሆነ ሊመረምሩ ፍቃደኛ ይሆናሉ ወይ? ሊገቡ ፍቃደኛ ይሆናሉ ወይ? የሚመረምሩ ሰዎች አደገኛ ችግር ውስጥ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ዋስትና የማንሰጣቸው ከሆነ፤ እንደዚህ አይነት risk ሊወስድ የሚችል አካል ላይኖር ይችላል” ሲሉ የፓርላማ አባሉ  በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ የፓርላማ አባሉ ላቀረቡት ጥያቄ አዘል አስተያየት ምላሽ ሲሰጡ “ለእንደዚህ አይነት የምርመራ ስራዎች ዋስትና የሚሰጥ ህግ” መኖሩን ጠቅሰዋል። “ዋስትና መስጠት እና ሌላ ነገር እንዲያደርግ ማድረግ የተለያየ ነገሮች ናቸው” ሲሉም ድንጋጌው መሰረዙ ተገቢ መሆኑን ደግፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]