የፓርላማው ያለፈው ዓመት ክራሞት እንዴት ነበር?

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘንድሮው ስራውን ዛሬ መስከረም 26፤ 2018 በይፋ ይጀምራል። የተመረጡበት ጊዜ ሊጠናቀቅ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ የቀራቸው የስድስተኛው ዙር የፓርላማ አባላት፤ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አቻዎቻቸው ጋር ሆነው የመጨረሻ የስራ ዘመናቸውን የመክፈቻ ስነ ስርዓት ዛሬ ከሰዓት በተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ይታደማሉ። በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት ህጎችን የማውጣት፣ የአስቸኳይ ጊዜ እና የጦርነት አዋጅ የማዋጅ ስልጣን የተሰጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለፈውን ዓመት እንዴት ነበር ያሳለፈው?። ተከታዩ ዳሰሳ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል።  


የፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለፈውን በጀት ዓመት ያሳለፈው ባተሌ ሆኖ ነበር። ፓርላማው በሳምንት ሁለት ጊዜ ማክሰኞ እና ሐሙስ ሊያደርጋቸው የሚገባቸውን ሁሉንም መደበኛ ስብሰባዎች ባያከናውንም፤ በአጠቃላይ 43 መደበኛ ስብሰባዎች እና ሶስት ልዩ ስብሰባዎች አካሄዷል።

በበጀት ዓመቱ ለምክር ቤቱ 56 ረቂቅ አዋጆች የቀረቡ ሲሆን ሰላሳ አራቱ ለቋሚ ኮሚቴዎች ተመርተው “ይፋዊ የህዝብ ውይይት” ከተደረገባቸው በኋላ ጸድቀዋል። ለምክር ቤቱ ከቀረቡ ረቂቅ አዋጆች መካከል አስራ አምስቱ ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግረው ይፋዊ የህዝብ ውይይት ሳይደረግባቸው የጸደቁ ናቸው። 

ፓርላማው ዘጠኝ ረቂቅ አዋጆችን ከ2017 ዓ.ም. ወደ 2018 ዓ.ም. አሸጋግሯል። ለዚህ ዓመት ከተሸጋገሩት መካከል ሁለት ረቂቅ አዋጆች ከካቻምና ወደ 2017 ዓ.ም የተላለፉ እንደነበሩ የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ለሚ በዶ ባለፈው ሐምሌ ወር ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ዓመት መርምሮ ያጸድቃቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ አዋጆች መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከተው ይገኝበታል። ይህ አዋጅ እና ባለፈው ሐምሌ ወር ፓርላማው ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የጸደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፤ በዚህ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል።  

የቀድሞው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና  የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ያወጣቸው አዋጆች “አፋኝ ናቸው” በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የቆዩ ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ በእነዚህ አዋጆች ላይ በዘርፉ ባለሙያዎች ጥረት ስር ነቀል ማሻሻያዎች እንደተደረጉባቸው ይታወሳል። 

ሆኖም በ2017 ዓ.ም. ከእነዚህ አዋጆች መካከል ሁለቱ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመልሰው በመምጣት ማሻሻያቸው እንዲጸድቅ ተደርጓል። ይህ ሂደት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት “አፋኝ” የሚባሉ ሕጎች እና አሰራሮችን በማሻሻል ያሳየውን አዎንታዊ እርምጃ “የቀለበሱ ናቸው” የሚል ትችት አስከትሏል።

ይህን መሰል ትችት ካስተናገዱት አንዱ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ነው። በ2013 ዓ.ም. በጸደቀው አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ የሆነ ግለሰብ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ቦርድ አባል እንዳይሆን ይከለክላል። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በፓርላማው በጸደቀው ማሻሻያ፤ ይህ ክልከላ ተሽሯል።

ማሻሻያው ከመጽደቁ በፊት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር እና የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን ጨምሮ ከ14 የሲቪል ድርጅቶች ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ባለፈው ዓመት ከጸደቁ ህጎች መካከል ሌላው ብርቱ ትችት አጋጥሞት የነበረው፤ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ነው።

አዋጁ ለውዝግብ መነሾ የሆነው “በሽፋን ስር” ስራውን ለሚያከናውን መርማሪ “ከግድያ በስተቀር” የሚፈጽማቸውን የወንጀል ድርጊቶች ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ድንጋጌ ማካተቱ ነበር። ድንጋጌውን የያዘው አዋጅ በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ ከጸደቀ ከ20 ቀናት በኋላ፤ የተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ አወዛጋቢውን አንቀጽ ሰርዞታል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2017 ዓ.ም ካጸደቃቸው አዋጆች ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ተግባራዊ ከሚያደርገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በቀጥታ የተገናኙ አዋጆች እና የብድር ስምምነቶች ይገኙበታል።  በታህሳስ 2017 ዓ.ም. የጸደቀው የባንክ ስራ አዋጅ፤ ለረዥም ዓመታት ተዘግቶ የቆየውን ገበያ ለውጪ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች በመክፈት ጉልህ የፖሊሲ ለውጥ በተጨባጭ ተግባራዊ ያደረገ ነው። 

ይሁንና በረቂቁ ላይ በተደረጉ ውይይቶች የፓርላማ አባላት የሰጧቸው አስተያየቶች፤ በጉዳዩ ላይ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አናሳ እንደሆነ ያሳበቀ ሆኖ አልፏል። አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የባንክ ስራ አዋጅን እና በተመሳሳይ ጊዜ የተሻሻለውን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲያምታቱ መታየታቸውም አስተዛዝቧል።

የተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን ከ845 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር የሚያዘዋውር አዋጅ ሲያጸድቅ፤ ብድሮቹን የፈቀዱ ተቋማት አመራሮች እና የክትትል እና ቁጥጥር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተጠያቂነት ጉዳይ ሳይነሳ መቅረቱም እንዲሁ አጠያያቂ ነበር። ፓርላማው በአዋጁ ላይ ባደረገው ውይይት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የከረረ ትችት ቢሰነዘርም፤ ህጉ በጸደቀበት ወቅት አንድ ድምጸ ተአቅቦ ብቻ ነበር የተመዘገበው። 

ፓርላማው ባለፈው ዓመት ካጸደቃቸው እና መነጋገሪያ ከነበሩ ህጎች መካከል፤ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው አዋጅ አንዱ ነው። የንብረት ማስመለስ አዋጅ፣ የኢሚግሬሽን አዋጅ እንዲሁም ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም የሚከለክለው አዋጅ ትኩረት ስበው ከነበሩ ህጎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። ከፍ ያለ ተጽዕኖ ያላቸው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ፣ የጤና አገልግሎት አዋጅ እና የፌደራል ገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅም የጸደቁት በ2017 ዓ.ም. ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)