ስስ ፌስታል መጠቀምን የሚከለክለው የአዋጅ ማሻሻያ፤ በፓርላማ የህዝብ ውይይት የተፈጻሚነት ጥያቄ ተነሳበት 

በቤርሳቤህ ገብረ

ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም የሚከለክለው አዲስ የአዋጅ ማሻሻያ፤ በአምራቾች ዘንድ የተፈጻሚነት ጥያቄ ተነሳበት። የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ፤ የፕላስቲክ ከረጢቶች በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት መታገዳቸውን በመጥቀስ “ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አዲስ የሚሆንበት ምክንያት የለም” ብሏል። 

ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶች ክልከላ ጉዳይ ያነጋገረው፤ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 17፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ ነው። የዛሬው ውይይት የተጠራው፤ ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ለፓርላማው በቀረበው “የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ” የአዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ ላይ የህዝብ አስተያየትን ለማድመጥ ነበር። 

በፓርላማ ለውይይት የቀረበው ማሻሻያ፤ ለ13 አመት በስራ ላይ የቆየውን አዋጅ የሚተካ ነው። ነባሩን የህግ ማዕቀፍ ማሻሻል ያስፈለገው፤ “በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ” እና “የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ተግባራትን ተከታትሎ ለማስፈጸም” በማሰብ እንደሆነ አዲሱን አዋጅ ለማብራራት የቀረበው ሰነድ ያስረዳል።

በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ለማሻሻል በምክንያትነት የተነሳው ሌላው ጉዳይ፤ ህጉ “በሀገር ውስጥ የሚገኙ ፕላስቲክ ምርት አምራቾችን ለመቆጣጠር ምቹ አለመሆኑ” ነው። አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ “ቁጥጥር የሚደረግባቸው” የፕላስቲክ ምርቶች “ውፍረታቸው ከ0.03 ሚሊሜትር በታች ብቻ መሆናቸውን” የጠቀሰው ማብራሪያው፤ “እነዚህን ለመለየት አስቸጋሪ በመሆኑ” ማሻሻያው ማስፈለጉን አመልክቷል። 

በፕላስቲክ ምርት ላይ የሚሰጠው ፈቃድ “ፕላስቲክ እና ጎማ” ተብሎ “በጠቅላላ” የሚሰጥ መሆኑ፤ “ለይቶ ለመቆጣጠር ከባድ” እንዳደረገው እና በተለይ በሀገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ “ተግዳሮት” የሚያስከትል እንደሆነ የአዋጅ ማሻሻያ ማብራሪያው በተጨማሪነት ገልጿል። በነባሩ አዋጅ ስለፕላስቲክ ቆሻሻ የተደነገገው “ማምረት ወይም ወደ ሀገር ማስገባት ብቻ መሆኑ” እና “ስለ አጠቃቀም ወይም አያያዝ በአግባቡ ያላካተተ መሆኑ የቁጥጥር ስርዓቱን ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉም በሰነዱ ላይ ተብራርቷል።

እነዚህን ክፍተቶች ለማሻሻል የተዘጋጀው አዲሱ አዋጅ፤ “ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀምን” ከልክሏል። “የፕላስቲክ ከረጢት” ማለት “አነስተኛ ጥግግት ያለው፣ በቀላሉ በስብሶ ከአፈር ጋር የማይዋሃድ እና ሌሎች ምርቶችን ለመያዝ የሚያገለግል” እንደሆነ በአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። 

ማንኛውም ሰው “የፕላስቲክ ከረጢት የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ በከተገኘ”፤ ከአምስት ሺህ ብር በማያንስ እና ከ10 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣም በአዲሱ አዋጅ ላይ ተደንግጓል

አዲሱ አዋጅ “የፕላስቲክ ከረጢት” የሚለውን አገላለጽ ጥቅም ላይ ያዋለው፤ “በተለምዶ ፌስታል የሚባለውን ምርት ለማመላከት” እንደሆነ በማብራሪያ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያው፤ የፕላስቲክ ከረጢት በሚያመርቱም ሆነ በሚጠቀሙ ግለሰቦች ላይ የሚከተለውን “የወንጀል ተጠያቂነት” የዘረዘረ ነው።

ማንኛውም ሰው” የፕላስቲክ ከረጢት ካመረተ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ካስገባ፣ ለገበያ ካቀረበ ወይም ከሸጠ፣ ለንግድ አላማ ካከማቸ ወይም ይዞ ከተገኘ”፤ ከአምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል። በዚህ ተግባር ላይ የተገኘ ሰው ከእስር ቅጣቱ በተጨማሪ “ከ50 ሺህ ብር በማያንስና ከ200 መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።  

እነዚህን “የወንጀል ድርጊቶች የፈጸመው” ህጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ፤ የገንዘብ ቅጣቱ ከላይ ከተመለከተው “ሶስት እጥፍ” እንደሚሆንም በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል። ማንኛውም ሰው “የፕላስቲክ ከረጢት የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ በከተገኘ”፤ ከአምስት ሺህ ብር በማያንስ እና ከ10 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣም በአዲሱ አዋጅ ላይ ተደንግጓል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዛሬው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ አምራቾች፤ በአዋጅ ረቂቁ የተቀመጡ ክልከላዎች ተፈጻሚነትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ፌስታል እና የተለያዩ የሪሳይክል ምርቶችን ከሚያመርት ድርጅት የመጡ አቶ በረከት ገብረህይወት የተባሉ ተሳታፊ፤ የፕላስቲክ ከረጢትን “እንዴት አድርገን ከህይወታችን ልናወጣው እንችላለን?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

አቶ በረከት ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት፤ በየዓመቱ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት የሚተገበረውን “የአረንጓዴ አሻራ” መርኃ ግብርን ነው። “እነዚህን የፕላስቲክ ከረጢት አምራቾች ‘ከስራ ውጡ’ ስንላቸው፤ በዓመት ከ10 እና 15 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የሚተከልበት የፕላስቲክ ማሸጊያን ማን ሊያመርት ነው?” ሲሉ አቶ በረከት ሌላ ጥያቄ ሰንዝረዋል። 

የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ምንተስኖት ለማ በበኩላቸው “የፕላስቲክ ፌስታል የምናስወጣው ምን አማራጭ ተቀምጦ ነው?” የሚል ጥያቄ አስከትለዋል። “እኛ ሀገር ጉሊትም ይሁን ሱፐርማርኬት፤ ጨው፣ ስኳር፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም የሚሸጠው እየተመዘነ ነው። ያንን አንጠልጥሎ መሄድ የሚቻለው በፌስታል ነው። ሌላ በጨርቅ ወይም በካኪ ወረቀት እናድርገው ብንል ተግባራዊ የሚሆን አይደለም” ሲሉ ሞግተዋል። 

የፕላስቲክ ከረጢት ወይም “ስስ ፌስታል” በውፍረታቸው ልክ “በሳይንሳዊ መንገድ” ተለክቶ በአዋጁ ላይ ቢቀመጥ፤ ለአፈጻጸም “ምቹ” እንደሚሆን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አመልክተዋል። ሌሎች ሀገራት ፕላስቲክን እንዳልከለከሉ ነገር ግን “አጠቃቀሙ ላይ ገደብ” እንዳደረጉ ያስረዱት አቶ ምንተስኖት፤ ይህ አካሄድ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ እንዲታይ ጠቁመዋል።

በፕላስቲክ ከረጢት የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ አቶ ሰይፈ ተፈራ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፤ “ፌስታል ይቁም የሚባለው ነገር አያስኬድም። ህዝብ እና መንግስት የሚያጋጭ ነው ይታሰብበት” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። መንግስት በዚህ ዓመትም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን አፍልቶ ለመትከል በዝግጅት ላይ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሰይፈ፤ የእርሳቸው ድርጅት የተወሰኑ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ለማምረት ጨረታ ማሸነፉን ገልጸዋል።

በፕላስቲክ ከረጢት ዘርፍ ላይ ብቻ 900 የሚደርሱ ፋብሪካዎች እንዳሉ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪው፤ ጉዳዩ ይበልጥ እንዲታሰብበት አሳስበዋል። “እኔ 250 ሰራተኛ አለኝ። ከዚያ ውስጥ 220 ሴቶች ናቸው። ይበተኑ ወይ?” ሲሉም አቶ ሰይፈ ጥያቄ አዘል አስተያየት አንስተዋል። 

በዛሬው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ወንደወሰን ታደሰ የተባሉ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የመጡ የስራ ኃላፊ፤ “የፕላስቲክ ከረጢትን እና የፕላስቲክ ማሸጊያን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል” ብለዋል። “ከችግኝ ጋር የተያያዘው የፕላስቲክ መጠቅለያ እንጂ ማሸጊያ እንደማይባልም” አስረድተዋል።

ለችግኝ መጠቅለያ የሚሆነው ፕላስቲክ አዋጁን ተከትሎ ወደፊት በሚወጣው መመሪያ “በልዩ ሁኔታ” “ይፈቀዳል፤ አይፈቀድም” የሚለው አንደሚወሰን አቶ ወንደወሰን ለተሳታፊዎች ተናግረዋል። የፕላስቲክ ከረጢት በውፍረት ተለክቶ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ እንዲከለከል የተደረገው ከሚያደርሰው ጉዳት አኳያ እንደሆነም አስረድተዋል።

በዛሬው የፓርላማ ህዝባዊ ውይይት ማጠቃለያ የመናገር ዕድል የተሰጣቸው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ፤ ከፕላስቲክ ከረጢቶች ውስጥ በጣም የተወሰኑቱ “መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉ” መሆናቸውን ገልጸዋል። አብዛኞቹ ፕላስቲክ ከረጢቶች “እዚህም እዚያም ተጥለው እንደሚገኙ” የገለጹት ሌሊሴ፤ ይህም “አደጋ እየፈጠረ” እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት፤ ከብቶች በየቦታው የተጣሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች በመብላት “እየሞቱ” መሆኑን ነው። የፕላስቲክ ከረጢቶች በቀላሉ የማይበሰብሱ በመሆናቸው፤ “አፈር እና ውሃ እየበከሉ” እንደሚገኙም ዋና ዳይሬክተሯ አክለዋል። 

እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ሞሮኮ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማገዳቸውን የጠቀሱት ሌሊሴ፤ “ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አዲስ የሚሆንበት ምክንያት የለም” ሲሉ ለጠያቂዎች ምላሽ ሰጥተዋል። አዲሱ አዋጅ “በአረንጓዴ ልማት” ጥቅም ላይ የሚውለውን “የችግኝ ማቀፊያ” እንደማይከለክል የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ መመሪያ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ወደፊት በመመሪያ ላይ እንደሚቀመጡ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)