በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ያሉ የጸጥታ ሁኔታዎችን መከታተል የሚያስችል “የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት” ሊዘረጋ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ያሉ የጸጥታ ሁኔታዎችን የሚከታተልበት “የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት” (early warning system) ለመዘርጋት ጥናት እያደረገ መሆኑን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ አስታወቁ። ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ስብሰባ የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ ስጋቶች መንጸባረቃቸውን የገለጹት ዋና ሰብሳቢዋ፤ ሆኖም “ምርጫው ይራዘማል የሚል ነገር እንደሌለ” መታወቅ አለበት ብለዋል።

ይህንን ያሉት ቦርዱ በረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ ተሳታፊዎች ጋር በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 17፤ 2018 ምክክር ባደረበት ወቅት ነው። ቦርዱ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳውን ዛሬ ለውይይት ከማቅረቡ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት ሰኞ በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊዎች ጋር ውይይት አድርጎበት ነበር። 

በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት ግንቦት 24 ድምጽ የሚሰጥበት ዕለት ይሆናል። ቦርዱ ይፋዊ የምርጫ ውጤት ለመግለጽ ያቀደው፤ ከድምጽ መስጪያው ዕለት ከአስር ቀናት በኋላ ማለትም ሰኔ 3፤ 2018 ነው። 

በጊዜ ሰሌዳው ላይ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና የሚሰጠው ጥቅምት 15 እንደሚሆን የተቀመጠ ሲሆን፤ ቦርዱ ይህንኑ ባለፈው ቅዳሜ አካሂዷል። ቦርዱ ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን በተመለከተ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ለማወያየት በሰነዱ ላይ ቀነ ቀጠሮ የያዘውም ለዛሬ ነበር። 

ግማሽ ቀን በፈጀው በዛሬው ምክክር፤ በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ እና ደህንነት ችግርን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ተሰንዝረዋል። ይህንኑ ችግር ያነሱ አንድ የመድረኩ ተሳታፊ፤ የጸጥታ ስጋትን በተመለከተ በመንግስት በኩል “ከፍተኛ”፣ “መካከለኛ” እና “ዝቅተኛ” በማለት የተለዩ ቦታዎች ስለመኖራቸው ጠይቀዋል።

እኚሁ ተሳታፊ ጥያቄውን ያቀረቡት “ጸጥታ እና ደህንነት ካልተረጋገጠ”፤ ማንም ወደ ቦታዎቹ ሄዶ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት አይችልም በሚል እሳቤ እንደሆነም አብራርተዋል። ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ፤ መስሪያ ቤታቸው የምርጫ ክልሎችን የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ መረጃዎችን ከክልሎች እንደሚቀበል አስረድተዋል።

በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የሚኖሩ የጸጥታ ሁኔታዎችን በተመለከተ ደግሞ ቦርዱ ሪፖርት የሚያገኝበትን ስርዓት ለመዘርጋት ጥናት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። “እስከ መራጮች ምዝገባ ድረስ ከደረሰልን፣ እሱን በቦታው ላይ ካደረግን፣ ምንም አይነት ችግር ሲኖር ከታች ጀምሮ ሲስተሙ እየተቀባበለ ዋና መስሪያ ቤት ላይ በቀጥታ የሁኔታውን ሪፖርት [እናገኛለን]። ከዚያ ደግሞ ሊወሰድ የሚገባውን የመፍትሄ እርምጃ አብሮ ምክረ ሃሳብ የሚሰጥ አቅርበናል” ሲሉ ሜላትወርቅ ስለ ስርዓቱ አብራርተዋል።

“የምርጫ አስፈጻሚዎቻችን ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ህብረተሰብ ክፍል በአጭር ኮድ ባለ ቁጥር ሪፖርት እየተቀበልን፣ ያንን እያመሳከርን፣ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃ ጥረት የምናደርግበትን ነገር እየሰራን እንገኛለን” ያሉት የቦርድ ዋና ሰብሳቢዋ፤ “እሱ ፈጥኖ አልቆልን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን ለእኛ በጣም ትልቅ ድጋፍ ይሆናል” ሲሉ መስሪያ ቤታቸው እየዘረጋ ያለውን ስርዓት አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

“የጸጥታ ሁኔታ በቀጣይነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ እየተነጋገርን፣ እየተባበርን፣ አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠር ሁላችንም እገዛ እና ጥረት እያደረግን፣ ያለማቋረጥ እየተከታተልን ተግባራዊ የምናደርግ ይሆናል” ሲሉም ሜላትወርቅ በዛሬው ስብሰባ ላይ አክለዋል። ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ በሰጠው መግለጫ፤ ዘንድሮ የሚካሄደውን ምርጫ የሚያደርገው “ፈቃጅ” እና “አስቻይ” ባሉባቸው የምርጫ ክልሎች እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም።   

በዛሬው ውይይት ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሌላ ተሳታፊ ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ውይይት፤ “ምርጫው መራዘም” ሃሳብ መቅረቡን መስማታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስልም እኚሁ ተሳታፊ ጠይቀዋል።

የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ወደ 65 የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በባለፈው ሳምንት ስብሰባ መሳተፋቸውን አንስተዋል። “ አስቻይ ሁኔታ አለ ወይ? ምርጫ ማድረግ እንችላለን ወይ? የሴኪዩሪቲ ጉዳይ ምን እያደረጋችሁ ነው? የሚል ጥያቄ ነው የተጠየቅነው” ሲሉ ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበረው ውይይት ላይ የተነሱ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።

“በዚህም እንግዲህ ዛሬ ለእናንተ እንደሰጠነው አግባብ ያለውን ምላሽ ሰጥተናል። ይሄ በጋራ የምናየው ጉዳይ ነው። በክትትል የምናየው ጉዳይ ነው። በሞኒተሪንግ የምናየው ጉዳይ ነው። ሁሉንም የባለድርሻ አካላት፤ መንግስትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ የክልል መንግስታትን፣ የጸጥታ ክፍሎችን ሁሉ ባካተተ መንገድ እየተደጋገፍን፣ እየተረዳዳን  አስቻይ ሁኔታ ባለበት ሁሉ ይህንን ምርጫ ለማካሄድ እየሰራን መሆናችንን ተናግረናል” ሲሉ ሜላትወርቅ አስገንዝበዋል። 

“እንደ ህብረተሰቡ አካል፣ ያንን ስጋት እንደምንጋራው አስረድተናል። ከዚህ ውጭ ግን ካላንደሩ ይሄኛው ይቀነስ፣ ይሄኛው ይጨመር፣ ይሄኛው አይስማማንም ይውጣ ወይም ሙሉ ለሙሉ ይሄንን ካላንደር አንቀበልም የሚል rejection አልነበረም”

ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ

“እንደ ህብረተሰቡ አካል፣ ያንን ስጋት እንደምንጋራው አስረድተናል” ያሉት የቦርድ ዋና ሰብሳቢዋ፤ “ከዚህ ውጭ ግን ካላንደሩ ይሄኛው ይቀነስ፣ ይሄኛው ይጨመር፣ ይሄኛው አይስማማንም ይውጣ ወይም ሙሉ ለሙሉ ይሄንን ካላንደር አንቀበልም የሚል rejection አልነበረም” በማለትም ያለፈውን ሳምንት ስብሰባ ውጤት አስረድተዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ “ስጋታቸውን ማንጸባረቃቸውን” እና ይህንኑ ቦርዱ መቀበሉን የገለጹት ሜላትወርቅ፤ በስተመጨረሻም ምርጫው “ይራዘማል የሚል ነገር እንደሌለ” የስብሰባው ተሳታፊዎች እንዲያውቁት አሳስበዋል። “ይህንኑ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ፣ በህገ መንግስት የተቀመጠ የምርጫ ሂደት ‘እንቀጥላለን’ ብለን፤ ዛሬም ከእናንተ ጋር ውይይት ቀጥለናል … በጥቂት ቀናት ደግሞ scheduleን መሰረት አድርገን፣ እየሰራን እንሄዳለን” ሲሉም ተደምጠዋል። 

ምርጫ ቦርድ በቀጣይ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር እንደ አስፈላጊነቱ ግንኙነቶች ሊያደርግ እንደሚችልም ዋና ሰብሳቢዋ ጥቆማ ሰጥተዋል። ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ባስቀመጠው ዝርዝር መሰረት፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ የሚያከናውነው የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ነው። ይህንኑ ተከትሎ ቦርዱ በዛሬው ዕለት ባወጣው የቅጥር ማስታወቂያ፤ በምርጫ ክልል አስፈጻሚነት የመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው አመልካቾች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)