የቀድሞው የኢዴፓ አመራር አቶ አብዱራህማን አህመዲንን ጨምሮ ሶስት የሽብር ተከሳሾች በዋስ ተለቀቁ

የአማራ ክልልን እና የፌዴራል መንግሥታትን በኃይል ለማስወገድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል የሽብር ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው ግለሰቦች መካከል ሶስቱ በዋስትና መለቀቃቸውን የተከሳሾቹ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። እያንዳንዳቸው 200 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከተለቀቁት ተከሳሾች ውስጥ የኢዴፓ ከፍተኛ አመራር እና የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ አብዱራህማን አህመዲን እንደሚገኙበት ጠበቃው ገልጸዋል።

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ አቶ አብዱራህማንን ጨምሮ በ23 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የመሰረተው በሰኔ 2016 ዓ.ም ነበር። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የክስ ሰነድ፤ ተከሳሾቹ “ንስር አማራ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት” በሚል ስያሜ “የአማራ ህዝባዊ ሀይል ፋኖ” ህቡዕ አደረጃጀትን በአዲስ አበባ ከተማ ላይ አደራጅተው እንደነበር ይወነጅላል።

ተጠርጣሪዎቹ በዚህ የህቡዕ አደረጃጀት አማካኝነት፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን መረጃ ሰብሰበው በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች በማስተላለፍ ጥቃት እንዲደርስ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል። በጥቃቱ 55 ሰዎች መገደላቸውን፣ 82 ሰዎች መታገታቸውን፣ 80 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በክስ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። 

በእዚሁ ጥቃት 13.6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ውድመት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ሰነዱ ያትታል። ተከሳሾቹ ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ውስጥ “ትላልቅ” የፌደራል መንግስት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ላይ በከባድ እና በነፍስ ወከፍ መሳሪያ የሽብር ጥቃት “በመፈጸም” ተወንጅለዋል። የሽብር ጥቃቱ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጭምር የተፈጸመ መሆኑም በክስ ሰነዱ ላይ ተመልክቷል። 

ሃያ ሶስቱ ተጠርጣሪዎች “ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር”፣ “የፋኖ ቡድን ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል በህገ መንግስቱ ስልጣን የያዘውን መንግስት በኃይል ከስልጣን ለማውረድ ሲሰናዱ የነበረ በመሆኑ በፈጸሙት የሽብር ወንጀል ተከስሰዋል” ሲል የፌደራል ዐቃቤ ህግ የመሰረተው ክስ ያስረዳል። 

ለእስር ከተዳረጉ ሁለት ዓመት ሊሞላቸው ከሶስት ወራት ያነሰ ጊዜ የሚቀራቸው ተከሳሾቹ፤ በቀረበባቸውን የሽብር ክስ ላይ  በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲከራከሩ ቆይተዋል። ክሱን ሲመለከት የቆየው የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ትዕዛዝ መስጠቱን የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ክሱ ተሻሽሎ ከቀረበ በኋላ፤ በከሳሽ እና በተከሳሾች መካከል ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ የዋስትና ክርክር መደረጉን ጠበቃው አስረድተዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት፤ ዐቃቤ ሕግ ባሻሻለው ክስ ላይ የጠቀሰው የጸረ – ሽብር ድንጋጌ የዋስትና መብት የማያስከለክል በመሆኑ ክሳቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ለሶስቱ ደንበኞቻቸው ዋስትና መፍቀዱንም አክለዋል።

ተከሳሾቹ በፍርድ ቤት እንዲያሲዙ የተላለፈባቸውን የ200 ሺህ ብር ዋስትና በመክፈል፤ በዚያኑ ዕለት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መለቀቃቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። ሆኖም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤቱ በር ላይ ሲጠብቋቸው ነበር በተባሉ “የፌደራል ፖሊስ አባላት” ተይዘው፤ ለቀናት ያሉበት ሳይታወቅ ቆይተው እንደነበር ጠበቃው አስታውሰዋል። 

ተከሳሾቹ በዋስትና መለቀቃቸውን በመቃወም ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱን በስተኋላ ላይ እንደተረዱም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። የዛሬ ሳምንት አርብ ታህሳስ 17፤ 2018 ይግባኙን የተመለከተው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት፤ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ማጽናቱንም የተከሳሾቹ ጠበቃ አስረድተዋል። 

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ካስተላለፈ ከአራት ቀናት በኋላ የቀድሞው የፓርላማ አባል አብዱራህማን፣ አብረዋቸው የተከሰሱት አቶ መኮንን ደሳለኝ እና ግዛቸው ታምር ባለፈው ማክሰኞ ታህሳስ 21፤ 2018 በዋስ ከእስር እንደተፈቱ አቶ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱ እና የዋስትና ጥያቄያቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገባቸው ቀሪ 20 ተጠርጣሪዎች፤ ጉዳያቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለታቸውን አክለዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዋስትና ይግባኙን ለመመልከት ለታህሳስ 27፤ 2018 ቀጠሮ መስጠቱንም ጠበቃው ገልጸዋል። የእነ አቶ አብዱራህማን የሽብር ክስን የሚመመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከየካቲት 24 እስከ የካቲት 25፤ 2018 የክስ መከላከያ እንዲያቀርቡ በበኩሉ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)