እስራኤል ለሶማሌላንድ ከሰጠችው የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና በኋላ ዛሬ የመጀመሪያውን ስብሰባ ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት “የት ደረሰ?” የሚል ጥያቄ አነሳ። በመደበኛ ስብሰባው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስም ሆነ ምክትሎቻቸው ከሶማሌላንድ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የዛሬ ሁለት ዓመት በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባህር ወደብን ለማልማት የሚያስችላት እንደሆነ ተገልጾ ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ መንገዱን የሚጠርግላት መሆኑም በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በምላሹ ራስ ገዝ ለሆነችው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር ዕውቅና እንድምትሰጥ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በወቅቱ ገልጸው ነበር። በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረውን ይህን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር ልትሆን እንደምትችል ተገምቶ ነበር።

ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ የነበረው ይኸው የመግባቢያ ስምምነት፤ ሶማሌላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቃቃር በማድረግ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት በቱርክ አሸማጋይነት በአንካራ ከተማ እልባት ካገኘ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና የመስጠቷ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።
በአንካራ ከተፈረመው ቃልኪዳን በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ አስቀድመው የደረሱበት ስምምነት ከምን እንደደረሰ ሳይታወቅ አንድ ዓመት ተቆጥሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠቷን ያወጀችው። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ጥያቄ ያቀረቡ የፓርላማ አባላት፤ ባለፈው አርብ ታኅሣሥ 17፤ 2018 እስራኤል ለሶማሌላንድ የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና መስጠቷን አጣቅሰዋል።
ጥያቄውን ካነሱት የፓርላማ አባላት አንዱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት እንደቀሩት አስታውሰዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ የ20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ በኪራይ ውል ማግኘት የሚያስችላት እንደነበር አንስተዋል።

በምትኩም ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት መካከል የመጀመሪያዋ በመሆን ለሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት ተስማማታ እንደነበር ገልጸዋል። ይሁንና ኢትዮጵያ “የባሕር በሩን ሳታገኝ እና ለሶማሌላንድ እውቅና ሳትሰጥ” በእስራኤል መቀደሟን ዶ/ር አበባው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት “ሁለተኛዋ ሀገር” ትሆን እንደሆነም የፓርላማ አባሉ ጠይቀዋል። ዶ/ር አበባው ሌላው ያነሱት ጥያቄ፤ ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጋር ስምምነት እያደረጉ መሆኑን የተመለከተ ነበር።
የፓርላማ አባሉ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት፤ “የደህንነታችን ስጋት” ሲሉ የጠሯት ግብፅ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ እና ከኤርትራ ጋር ስምምነት ያደረገቻቸውን ስምምነቶች ነው። ግብፅ “ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት እንዳደረገች እና በቅርቡ ከጅቡቲ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟ እየተነገረ ነው” ሲሉ ዶ/ር አበባው አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ጥቅምት ወር ግብፅ እና ኤርትራ “ስለ ባህር ኃይል አጠቃቀም” ስምምነት ላይ እንደደረሱ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡን አንስተዋል። “ታዲያ እኛ ከአንዳቸውም ሀገራት ጋር የተጨበጠ የወደብ መብት ሳናገኝ፣ በሚዲያ ብቻ እያወራን የበይ ተመልካች ሆነን የምንቀጥለው እስከ መቼ ነው?” በማለት ጠይቀዋል።
ዶ/ር አበባው ሌላው ያነሱት ጉዳይ “ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሄደብንን እና የህልውና ጉዳይ” ያሉትን የአሰብ ወደብ የማስመለስ አጀንዳን ነው። የአሰብ ወደብን ለማስመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለማቀፍ ሕጎችን እና ዲፕሎማሲን ተጠቅሞ ስለሰራው ሥራ የፓርላማ አባሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
“በዚህ ጉዳይ በመድከማችን ይመስላል ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦራቸውን ወደ ድንበር ያስጠጉት እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል የቃላት ጦርነት እየተካሄደ ያለው” ሲሉም ዶ/ር አበባው አክለዋል። መንግሥት የባሕር በር ፍላጎትን ለማሳካት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ሌላ የተወካዮች ምክር ቤት አባልም ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ለማሳካት ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ያስታወሱት አቶ ካሚል ሀሺም የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ይህን ስምምነት ወደ ተግባር ከመቀየር አንጻር “ምን የተሠራ ሥራ አለ? የወደፊት እጣ ፈንታውስ ምን ሊሆን ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለፓርላማ አባላቱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት የተቆጠቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን፤ ኢትዮጵያ “ከአብዛኛዎቹ” ጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት “ጥሩ የሚባል” መሆኑን ተናግረዋል። “አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ተግባብተን በጋራ ነው የምንሰራው” ሲሉም ተደምጠዋል።
በአንዳንድ ሀገራት ውስጥ ያሉ የእርስበርስ ግጭቶች፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ ሀገራት እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ላይ “የሚያጠላው ጥላ” ስለመኖሩ ዶ/ር ጌዲዮን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። ከግጭቶቹ በተጨማሪም ቀጠናው ኃያላንም ሆኑ በመካከለኛ ረድፍ የሚሰለፉ ብዙ ሀገራት “አይናቸውን የጣሉበትና የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሻኮቱበት” የመሆኑ ጉዳይ፤ ለአካባቢው ሀገራት ግንኙነት ፈተና መሆኑንም አስረድተዋል።

የወደብ እና የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ “ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ግንኙነት እና ትስስር ስትራቴጂያዊ የሆነ የረጅም ጊዜ ጥቅማችንን እና ትልማችንን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ላሰምርበት እፈልጋለሁ” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው፤ “ለረጅም ጊዜ ታቅዶበት፣ ታስቦበት በተሰራ ሴራ” እንደሆነም ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ እና ለማስተካከል “የረጅም ጊዜ እይታ ያስፈልጋል” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮን ነገሩ በአጭር ጊዜ የሚፈታ ጉዳይ አለመሆኑን አመልክተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ፍትሃዊ እና ተገቢ” ያሉት የባሕር በር ጥያቄ፤ “እንዴት እውን መሆን አለበት?” ወደሚለው “ምዕራፍ ተሸጋግረናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ጥያቄው እንዴት እውን ይሁን የሚለው “ብዙ ነገሮችን ታሳቢ ማድረግ” እንዲሁም “ብዙ ትግልና ልፋት” የሚጠይቅ እንደሆነ በመግለጽ፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። “ይሄ ጉዳይ የአንድ መንግስት ጉዳይ ብቻ አይደለም ማለት ነው። ይሄ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የፓርቲ መስመርን የሚሻገር በውስጥ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን የሚያልፍ፣ የሚሻገር ጉዳይ ነው” ሲሉም ሁሉም በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
“[የባሕር በር ጥያቄ] ጉዳይ የአንድ መንግስት ጉዳይ ብቻ አይደለም ማለት ነው። ይሄ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የፓርቲ መስመርን የሚሻገር በውስጥ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን የሚያልፍ፣ የሚሻገር ጉዳይ ነው”
ኢትዮጵያ ከምታነሳው የባሕር በር ጥያቄ ጋር በተገናኘ፤ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ በተለያዩ ጊዜያት ስጋታቸውን በመግለጽ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የባሕር በር ጉዳይን ያካተተው የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት፤ በስተኋላ ላይ የተነሳው የአሰብ ጉዳይ ለስጋቶቹ በመነሻነት ይጠቀሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































