በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያገኘ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር፤ ለቀጣዩ ምርጫ 1,200 ገደማ ዕጩዎችን ማዘጋጀቱን አስታወቀ

“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተባለው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅንጅት ምዝገባ ምስክር ወረቀት አገኘ። የቅንጅቱ አካላት የሆኑ አራት ፓርቲዎች፤ በመጪው ምርጫው የሚወዳደሩ 1,200 ገደማ ዕጩዎችን አስቀድመው ማዘጋጀታቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“ለኢትዮጵያ” በሚለው አጭር ቃል የሚጠራው ይኸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፤ መመስረቱ ይፋ የተደረገው ባለፈው መስከረም ወር ነበር። ቅንጅቱን የመሰረቱት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ)፣ እናት ፓርቲና እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ የተባሉ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው።

አምስቱ ፓርቲዎች ቅንጅቱን የመሰረቱት “ሕዝቡ ተሰባሰቡ ወይም ተሰባበሩ ስላለን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ምክር ተቀብለን ነው” ሲሉ አንድ የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በምርጫ 97 ከነበረው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅንጅት ተሞክሮ በመውሰድ የተመሰረተው ይኸው የፓርቲዎች ስብስብ፤ “የመራጮች ድምጽ እንዳይከፋፈል” በማድረግ በመጪው ምርጫ “ጠንካራ ተፎካካሪ” የመሆን ዓላማ አለው።

ለእዚህ የፓርቲዎች ቅንጅት ምርጫ ቦርድ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ያዘጋጀው ህዳር 5፤ 2018 ቢሆንም፤ ለፓርቲዎቹ የደረሰው ግን ባለፈው ሰኞ ታህሳስ 20 መሆኑን ኢሕአፓ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። ከምዝገባ የምስክር ወረቀቱ ጋር ተያይዞ ለፓርቲዎቹ የተላከው የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ፤ በቅንጅቱ መንቀሳቀስ የሚችሉ አራት ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን ይገልጻል።

ቦርዱ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር “ቅንጅት ለመመስረት የሚያስችለውን በአዋጅ የተቀመጠ መስፈርት አላሟላም” ያለውን እናት ፓርቲን ለጊዜው ከትብብሩ ውጭ አድርጎታል። እናት ፓርቲ ቅንጅቱን ለመመስረት የወሰነበትን ጉባኤ ያደረገው “ባልተሟላ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት” መሆኑን እና “ከአባላት የቀረበ ተቃውሞም” መኖሩን በመግለጽ ነው ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ጥያቄ ያልተቀበለው። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ፤ “የእናት ፓርቲ ላዕላይ ምክር ቤት ለሁሉም የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ጥሪ በማድረግ እና መድረክ በማዘጋጀት የመቀናጀት ጉዳይ ላይ በመወያየት ውሳኔ ማሳለፍ ይገባዋል” ሲል ያዝዛል። “በዚህ አግባብ የላዕላይ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ወስኖ ሰነድ ሲያቀርብ፤ [እናት ፓርቲ] በቅንጅት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የቅንጅቱ አካል መሆን ይችላል” ሲልም ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።   

የእናት ፓርቲ ጉዳይም እልባት እንዲያገኝ ቅንጅቱ ከፓርቲው ጋር ጥረት እያደረገ መሆኑን የኢሕአፓው አመራር ገልጸዋል። ይህ ካልሆነ ግን “የመራጮች ድምጽ መከፋፈል እንዳይፈጠር” እናት ፓርቲ በሚወዳደርበት ቅንጅቱ እንዳይወዳደር እና ቅንጅቱ በሚወዳደርበት ደግሞ እናት ፓርቲ እንዳይወዳደር ለማድረግ “እየተዘጋጀን ነው” ሲሉም አመራሩ አስረድተዋል።

“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በቀጣዩ የ2018 ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የወሰነው የምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት ከመድረሱ በፊት እንደሆነ እኚሁ የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር ገልጸዋል። ቅንጅቱ በምርጫው ለመሳተፍ የወሰነው “አስቻይ ሁኔታ ኖሮ አይደለም” የሚሉት እኚሁ አመራር፤ ሆኖም ቅንጅቱ ራሱን ከምርጫው ከማግለል ይልቅ በምርጫው በመሳተፍ “አስቻይ ሁኔታዎች እንዲኖሩ” ለመታገል መምረጡን ተናግረዋል።

የቅንጅቱ አካላት የሆኑት አራት ፓርቲዎች፤ ከምርጫ ቦርድ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ከማግኘታቸው በፊት ዕጩዎችን በማዘጋጀት በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል። ፓርቲዎቹ ለምርጫው 1,200 ገደማ ዕጩዎችን ማዘጋጀታቸውንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። 

ቅንጅቱ “በጣም አስቸጋሪ እና ጦርነት ካለባቸው” አካባቢዎች በስተቀር፤ በሁሉም አካባቢዎች ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ማዘጋጀቱን የኢሕአፓው አመራር ገልጸዋል። በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት ቅንጅቱ በከተሞች እና በአንዳንድ ቦታዎች ብቻ ዕጩዎች ማዘጋጀቱን አመራሩ አክለዋል።  

የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ቅንጅት በኦሮሚያ ክልል “ግጭት ካለባቸው ጥቂት ቦታዎች” በስተቀር በአብዛኛው አካባቢዎች ዕጩዎች ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል። በሌሎች ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ግን የቅንጅቱ  ዕጩዎች “በተሟላ መልኩ” እንደተዘጋጁ አመራሩ አስረድተዋል። ቅንጅቱ ዕጩዎቹን በመጪው ሰኞ ለምርጫ ቦርድ እንደሚያቀርብም የኢሕአፓው አመራር ጠቁመዋል።

“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” “ጦርነቶች እንዲቆሙ፣ የታሰሩ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ ገለልተኛ አስመራጮች እንዲዘጋጁ፤ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እንዲኖሩ” የሚሉ እና ሌሎችንም መስፈርቶች ለምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ማቅረቡን አመራሩ አስታውሰዋል። እነዚህ መስፈርቶች የማይሟሉ ከሆነ፤ ቅንጅቱ በሂደት “ሌላ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል” ሲሉም ቀጣይ ሂደቶች መጪውን ጊዜ የሚወስኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)