የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በአምስት ዓመት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ አዲስ ዋና ዳይሬክተር ሊሾምለት ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ወ/ሮ ሐይማኖት ዘለቀን በዕጩነት አቀረቡ። ላለፉት 23 ዓመታት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና የመንግስት ተቋማት የሰሩት የወ/ሮ ሐይማኖት ሹመት፤ ነገ ማክሰኞ ታህሳስ 28፤ 2018 በሚካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፤ መገናኛ ብዙኃን ተግባራቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን መስሪያ ቤት ነው። ላለፈው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተቋሙን የመምራት እና የማስተዳደር ኃላፊነት ተረክበው ሲሰሩ የቆዩት ዶ/ር ሳምሶን መኮንን ነበሩ። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን እና አለምአቀፋዊነት ጽህፈት ቤትን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ሳምሶን፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት ባለፈው ዓመት ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

በ2013 ዓ.ም. በአዋጅ የተመሰረተው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ሁለተኛ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ሳምሶን፤ እስካለፈው ሳምንት ድረስ በስራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ  “በገዛ ፍቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸውንም” እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መስሪያ ቤቱን የሚመራ አዲስ ዋና ዳይሬክተርን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደብዳቤ የጻፉት ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 23፤ 2018 ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይኸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ሐይማኖት ዘለቀ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲሾሙ እጠይቃለሁ” ይላል። 

በደብዳቤው የተጠቀሰው የአዋጅ ድንጋጌ “የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምሎ በመንግስት አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል” ይላል። ሆኖም ባለፈው ሚያዝያ ወር በፓርላማ የጸደቀው የእዚሁ አዋጅ ማሻሻያ፤ ይህንን ድንጋጌ በመሰረዝ በአዲስ ተክቶታል።

አዲሱ ድንጋጌ “የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል” ይላል። ይህ የአዋጅ ማሻሻያ በ2013 በነበረው አዋጅ ለመስሪያ ቤቱ ቦርድ ተሰጥቶ የነበረውን፤ የዋና ዳይሬክተር ዕጩን የማቅረብ ዕድል የሻረ በመሆኑ ትችት ቀርቦበት እንደነበር አይዘነጋም።

ይህን ትችት የሚያቀርቡት ወገኖች፤ ቦርዱ የዋና ዳይሬክተር ዕጩን የመጠቆም ዕድል ማግኘቱ “ለስራው አግባብነት ያለው ዝግጁነት ያላቸውን ባለሙያዎችን ለማቅረብ የሚያስችለው” መሆኑን ያነሳሉ። ይህም ደግሞ “በቦርዱ እና የመስሪያ ቤቱን የዕለት ከዕለት ስራውን በሚመራው ዋና ዳይሬክተር መካከል የተሻለ የስራ ግንኙነትን የመፍጠር ዕድልን ያሰፋ ነበር” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። 

እነዚሁ ወገኖች “የቦርዱ አባላት የተለያየ ልምድ እና ውክልና ያላቸው በመሆናቸው፤ ብዝሃነትን እና አቅምን ያገናዘበ ምርጫ የማቅረብ ያስችላቸው ነበር” በማለት የቀድሞውን ድንጋጌ ይደግፋሉ። አዲሱ ድንጋጌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በፖለቲካ ስሌት ብቻ ተመርተው ዕጩ እንዲያቀርቡ በር የሚከፍትላቸው ነው” ሲሉም ይነቅፋሉ። 

አዲሱ ድንጋጌ በ2013 በወጣው አዋጅ የተካተተውን የዋና ዳይሬክተር አሿሿም ድንጋጌን ቢሽረውም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወካዮች ምክር ቤት በላኩት የሹመት ደብዳቤ ላይ ግን ተጠቅሷል። ነገ ማክሰኞ ታህሳስ 28፤ 2018 መደበኛ ስብሰባውን የሚያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ይህንን የሹመት ጥያቄ መርምሮ እንዲያጸድቅ አጀንዳ ተይዞለታል። 

በተሻረ ድንጋጌ የሹመት ጥያቄያቸው ለፓርላማ የቀረበው ወ/ሮ ሐይማኖት፤ በመገናኛ ብዙሃን በጋዜጠኝነት እና በአዘጋጅነት እንዲሁም በመንግስት ተቋማት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሰርተዋል። ወ/ሮ ሐይማኖት ለአዲሱ ሹመት ከመታጨታቸው አስቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ።

አዲሷ ተሿሚ በውጭ ቋንቋ  እና ስነ ጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሶሾሎጂ (ህንድ ከሚገኘው ኢንዲራ ጋንዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ ይዘዋል። ለፓርላማ የቀረበው የተሿሚዋ የስራ ልምድ እንደሚያመለክተው፤ ወ/ሮ ሐይማኖት የጋዜጠኝነት ስራ የጀመሩት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነው።

ወ/ሮ ሐይማኖት በኢዜአ በቆዩባቸው አምስት ዓመት የተጠጋ ጊዜ፤ ከሪፖርተርነት ጀምሮ እስከ አዘጋጅነት ድረስ ሰርተዋል። ጋዜጠኛዋ ከኢዜአ በኋላ በተቀላቀሉት የቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስቴር፤ ለሁለት ዓመት ያህል የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቡድን አስተባባሪ ነበሩ።

ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከፈረሰ በኋላ በተቋቋመው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በዋና ዳይሬክተርነት የሰሩት ወ/ሮ ሐይማኖት፤ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም (ኢቢሲ) በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ማገልገላቸው በስራ ልምዳቸው ላይ ሰፍሯል። 

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተዘዋወሩት አዲሷ ተሿሚ፤  በአስተዳደሩ ቢሮዎች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል። ወደ ከተማይቱ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ከመምጣታቸው አስቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እና የከተማዋ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]