በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ለውድድር የሚቀርቡ ዕጩዎች እና መራጮች በዲጂታል አማራጭ መመዝገብ የሚችሉበት መተግበሪያ እና የድረ ገጽ አማራጭ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። የዲጂታል አማራጮቹ፤ በስድስት የሀገሪቱ ቋንቋዎች ምዝገባ ለማከናወን እንዲችሉ ተደርገው መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 27፤ 2018 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ይፋ ማድረጊያ ስነ-ሥርዓት ላይ ነው። የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓቱ የሚያገለግለው ለመመዝገብ ብቻ መሆኑን በስነ-ሥርዓቱ ላይ የገለጹት የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ድምጽ ለመስጠት ግን ሁሉም መራጭ እንደወትሮው የተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ መሄድ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
ምርጫ ቦርድ ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ይፋ ባደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጪያ ዕለት ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 ነው። ይኸው የጊዜ ሰሌዳ፤ የዕጩዎች ምዝገባ ከፊታችን አርብ ጥር 1 እስከ የካቲት 1 ድረስ ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን አስቀምጧል።
በቴክኖሎጂ የሚደረገው የመራጮች ምዝገባ ከመጪው ጥር ወር አጋማሽ እስከ መጋቢት 7 ድረስ እንደሚደረግም በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተዘርዝሯል። ይህንን ምዘገባ ለማድረግ መራጮች “ምርጫዬ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን መተግበሪያ በሞባይል ስልካቸው ወይም በሌሎች መተግበሪያ በሚቀበሉ የኤሌክትሮኒክስ አማራጮች አውርደው መጠቀም እንደሚችሉ ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ለምዝገባ ተብሎ በቦርዱ በተዘጋጀው ድረ ገጽ በመግባት ምዝገባ ማከናወን እንደሚቻል ቦርዱ በዛሬው ሥነ-ሥርዓት ላይ ገልጿል። በምርጫው የሚሳተፉ ተወዳዳሪ ዕጩዎች በመተግበሪያውም ሆነ በጽረ ገጹ መመዝገብ እንደሚችሉም ቦርዱ አመልክቷል። እነዚህ የዲጂታል መመዝገቢያ አማራጮች በየትኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ወደ ፊት በዝርዝር እንደሚያሳውቅ ምርጫ ቦርድ አመልክቷል።
መራጮች እና ዕጩዎች “በማንኛውም ስፍራ እና ሰዓት” መመዝገብ ከሚችሉበት የዲጂታል አማራጭ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ በምርጫ ጣቢያዎችም በመቅረብ ምዘገባ ማከናወን የሚችሉበት አካሄድ ዘንድሮም ተግባራዊ ይሆናል። በዚህ መልኩ የሚደረገው የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሚሆነው እና ዛሬ ይፋ የተደረገው የዲጂታል ምዝገባ አማራጭን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ከስምንት ወር እንደወሰደ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ተናግረዋል። የዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱ፤ “ለአካታችነት” እና “ተደራሽነት” ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ “የዕጩዎችን እና የመራጮችን ጊዜ እንደሚቆጥብ”፤ “አላስፈላጊ ምልልሶችን እንደሚያስቀር” እንደዚሁም “ወጪ እንደሚቆጥብ” ሜላትወርቅ አስረድተዋል።
መራጮች ከዘንድሮው ምርጫ ጀምሮ ቋሚ የመራጭ ቁጥር እንደሚሰጣቸውም የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በዛሬው ሥነ-ሥርዓት ላይ ገልጸዋል። ይህ ቁጥር አንድ መራጭ ከሀገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በህይወቱ ዘመን ሁሉ በሚሳተፍባቸው ማናቸውም በቦርዱ የሚመሩ ምርጫዎች ላይ ድምጽ መስጠት የሚያስችለው እንደሆነም ዋና ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























