በአማራ ክልል ያሉ የጤና ባለሙያዎችን በውሰት በማዘዋወር ማሰራት “ላልተወሰነ ጊዜ” ታገደ 

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ባለሙያዎችን በውሰት የማዘዋወር አሠራር ከነገ ጥር 1፤ 2018 ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” መታገዱን አስታወቀ። የቢሮው አንድ የሥራ ኃላፊ፤ የውሰት ዝውውር ላልተወሰነ ጊዜ የታገደው “ከመመሪያ ውጭ የሆኑ” እና “ያልተገቡ አሠራሮች” በመስተዋላቸው መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ እገዳውን ያስተላለፈው፤ “የውሰት ዝውውርን በተመለከተ” ባለፈው ሰኞ ታኅሳስ 27፣ 2018 በጻፈው ደብዳቤ ነው። በክልሉ ዞኖች እና የከተማ አስተዳደሮች ስር ላሉ ጤና መሪያዎች እና ሆስፒታሎች የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፤ የመንግሥት ሠራተኞች የምልመላና መረጣ መመሪያን መሰረት በማድረግ የጤና ባለሙያዎች ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም በውሰት በመዛወር ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሷል።

በደብዳቤው የተጠቀሰው መመሪያ፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ” አንድን ሠራተኛ ከመንግሥት ልማት ድርጅት፣ ከክልል መንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት “ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ” በውሰት አዘዋውረው እንዲያሰሩ ይፈቅዳል። ሠራተኛው የውሰት ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደነበረበት መሥሪያ ቤት የመመለስ ግዴታ እንዳለበትም መመሪያው ይደነግጋል። 

ፎቶ፦ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

ሆኖም በተጨባጭ የሚታየው አሠራር፤ ከአምስት ዓመት በፊት የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አሻሽሎ ያወጣውን ይህ መመሪያ ያላከበረ ሆኖ ተገኝቷል። የክልሉ ቢሮ ጤና ባለፈው ሰኞ የጻፈው ደብዳቤም፤ ይህንኑ አመልክቷል። 

እንደ ቢሮው ገለጻ ከሆነ፤ መመሪያውን መሰረት በማድረግ ወደ ሌላ ተቋም የተዘዋወሩ ባለሙያዎች የቆይታ ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቀድሞ መሥሪያ ቤታቸው “የመመለስ ፍላጎት የላቸውም”። እነዚሁ ባለሙያዎች በተዘዋወሩበት ተቋም “በቋሚነት ለመቀጠል” “ዝውውር እንዲሰጣቸው” እንደሚፈልጉም ቢሮው በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

እነዚህን መሰል የባለሙያዎች ጥያቄዎች “ከመመሪያ ውጭ” እና “ያልተገቡ” መሆናቸውን በደብዳቤው የገለጸው ቢሮው፤ በአሠራሩ ላይ “ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረ” መሆኑንም አስታውቋል። በዚህም መሰረት “የውሰት ዝውውር አሰራር” ከነገ አርብ ጥር 1 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በመሆኑ ሁሉም ተጠሪ ተቋማት ይህንኑ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አዝዟል። 

ፎቶ፦ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ያሉ እና ውሳኔውን በቅርበት የሚያውቁ አንድ የሥራ ኃላፊ፤ ቢሮው የእገዳ ውሳኔውን ካስተላለፈባቸው ምክንያቶች አንዱ በክልሉ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር የተነሳ የዝውውር ፈላጊዎች መበርከታቸው እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል። “ምንም የሰው ኃይል እጥረት በሌለባቸው” የሥራ መደቦች ላይ ባለሙያዎችን በውሰት አዘዋውሮ ማሠራት መብዛቱም፤ ለእገዳው መተላለፍ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ኃላፊው አክለዋል።

የውሰት ዝውውር የሚፈቀደው “በጣም እጥረት ያለበት” እና “በመደበኛ ቅጥር ሲወጣ በቀላሉ ሊገኝ የማይቻል” እንደ ራዲዮሎጂና የቀዶ ጥገና ያሉ የሙያ መደቦች ላይ ብቻ መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል።  ሆኖም “በጣም በርካታ ተቋማት” መመሪያውን ተገን በማድረግ፤ “ብዙ ባለሙያዎችን በውሰት እየጋበዙ” ከአንድ ዓመት በኋላ ቋሚ እንዲሆኑ ጥያቄ ማቅረባቸው በአሰራር ላይ ችግር መፍጠሩን ኃላፊው ገልጸዋል።

ባለሙያዎችም በተመሳሳይ በውሰት የተዘዋወሩበት ቦታ ላይ “ኑሮ በመጀመራቸው”፤ ቀድሞ ወደነበሩበት ተቋም መመለስ “የማኅበራዊ ቀውስ” እንደሚፈጥርባቸው በማንሳት ቋሚ ዝውውር እንዲፈቀድላቸው እንደሚጠይቁ አስረድተዋል። በውሰት የተዘዋወሩ ባለሙያዎች ወርሃዊ ደመወዛቸው ቀድሞ በነበሩበት ተቋም እንደሚከፈል፤ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ግን በተዘዋወሩበት ተቋም እንደሚሸፈን ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፎቶ፦ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

ሆኖም ባለሙያዎቹ የቆይታ ጊዜያቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ደመወዛቸው በውሰት ከሄዱበት ተቋም ያልተመደበ በጀት ላይ መከፈሉ፤ በክልሉ ጤና ቢሮ የበጀት ክፍል ጥያቄ እንዲነሳ ያደረገ ጉዳይ ሆኖ እንደነበርም አውስተዋል። አሰራሩ በተወሰኑ የክልሉ ተቋማት ውስጥ የባለሙያ ክምችት እንዲኖር በአንጻሩ በሌሎች ተቋማት ላይ ክፍተት መፍጠሩንም አክለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የውሰት ዝውውርን ለጊዜው ቢያግድም “እጥረት አለባቸው” ተብለው በሚታሰቡ የሙያ መደቦች አንጻር ላይ ግን ጉዳዩ ሊታይ የሚችልበት አግባብ መኖሩን ገልጿል። ተጠሪ ተቋማት “የውጭ”፣ “መደበኛ” እና “የእርስ በእርስ ዝውውር እና ቅጥር” በራሳቸው ማድረግ ቢሮው ውክልና ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)