የሽብር ወንጀል ተከሳሾቹ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሃንስ ቧያለው፤ ያለመከሰስ መብታቸው ከህግ ውጪ መነሳቱን ለፍርድ ቤት አስረዱ። ተከሳሾቹ በዐቃቤ ህግ የቀረቡባቸው ማስረጃዎች ውድቅ ተደርገው “በነጻ እንዲሰናበቱ” ጠይቀዋል።
ሁለቱን ተከሳሾች ይህን ጥያቄ ያቀረቡት፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 19፤ 2018 ላስቻለው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ነው። ችሎቱ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው፤ በዐቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃዎች ላይ በእነ አቶ ዮሃንስ ቧያለው መዝገብ ስር የሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች የጽሁፍ አስተያየት አጠናቅቀው እንዲያቀርቡ ነበር።
ተከሳሾቹ አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡ መጀመሪያ ቀጠሮ ተሰጥቿው የነበረው፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የችሎት ውሎ ነበር። ሆኖም የተከሳሾቹ አስተያየት በጊዜው ተጠናቅቆ ባለመድረሱ፤ የተከሳሽ ጠበቆች ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ባመለከቱት መሰረት ችሎቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዛሬው የችሎት ውሎ፤ በዐቃቤ ህግ የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ተከሳሾቹ ባለ 31 ገጽ ምላሻቸውን በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርበዋል። በዚህ ምላሽ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል፤ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሀንስ ያለመከሰስ መብታቸው “ከህግ ውጪ የተፈጸመ ነው” የሚለው ይገኝበታል።
ተከሳሾቹ በዚሁ መከራከሪያቸው፤ ያለ መከሰስ መብታቸው በየምክር ቤቶቹ አባላት በአብላጫ ድምጽ ስለመጽደቁ በዐቃቤ ህግ የማስረጃ ሰነድ ላይ መጠቀሱን አንስተዋል። ሆኖም በወቅቱ በየምክር ቤቶች ስብሰባዎች ላይ “ተገኝተዋል” የተባሉት አባላት ብዛት፤ ከጠቅላላ የምክር ቤቶቹ አባላት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር “አነስተኛ” መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ምክንያት በየምክር ቤቶቹ የተላላፈው ውሳኔ “ስህተት መሆኑን” ሁለቱ ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ አቤት ብለዋል። የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ለችሎቱ ያቀረቡት የጽሁፍ አቤቱታ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ሁለት ሶስተኛ የምክር ቤት አባላት የድጋፍ ድምጽ የሚያስፈልገው እንደሆነ በህገ-መንግስቱ ላይ መደንገጉን ይጠቅሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ድጋፋቸውን የሰጡ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር “332” እንደነበር የገለጸው የአቶ ክርስቲያን መከራከሪያ፤ ይህም ከሚፈለገው በታች እንደሆነ ይሞግታል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለው አጠቃላይ የመቀመጫ ብዛት 547 ነው።
በተመሳሳይ መልኩ መጋቢት 5፤ 2016 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የአቶ ክርስቲያንን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት በስብሰባው የተገኙ አባላት ቁጥር 245 መሆኑን አቤቱታው ጠቅሷል። በስብሰባው በአካል ከተገኙ የፓርላማ አባላት ውስጥ ሁለቱ ውሳኔውን ሲቃወሙ፤ ሌሎች ሁለት ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ ስለማድረጋቸው የስብሰባውን ቃለ ጉባኤ ዋቢ በማድረግ አቶ ክርስቲያን በጽሁፍ በሰጡት አስተያየት ላይ አስፍረዋል።
ምክር ቤቱ ስብሰባ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ዝቅተኛውን “276 የአባላት ቁጥር ሳያሟላ” ባደረገው ስብሰባ፤ ውሳኔውን “በ241 የድጋፍ ድምጽ” ማጽደቁን አቶ ክርስቲያን በጹሁፍ መከራከሪያቸው ላይ አመልክተዋል። የተወካዮች ምክር ቤት “ምልዓተ ጉባኤው ሳይሟላ” ባደረገው ስብሰባ፣ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ያሳለፈው ውሳኔ፤ “ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን የሚጻረር ነው” የሚል መከራከሪያ አቶ ክርስቲያን ለችሎቱ አቅርበዋል።
የሽብር ወንጀል ክሱ በስማቸው የሚጠራው አቶ ዮሃንስም፤ ተመሳሳይ መከራከሪያ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል። አባል የሆኑባቸው የአማራ ክልል እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች፤ እርሳቸውን አስመልክቶ ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች “ህግን ተከትለው የተፈጸሙ እንዳልሆኑ” ተናግረዋል።
አቶ ዮሃንስ የተያዙት “ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ” መሆኑን ገልጸው፤ በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ከለላቸው የተነሳውን የምክር ቤቱን የአሰራር እና የስነ ምግባር ደንብ ድንጋጌዎችን በጣሰ መልኩ መሆኑን ለችሎቱ አመልክተዋል። የክልሉ ምክር ቤት የካቲት 13 እና 14፤ 2016 ባደረገው ጉባኤ፤ የአቶ ዮሃንስ ያለ መከሰስ መብት እንዲነሳ በሶስት ድምጸ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ስለመጽደቁ በቃለ-ጉባኤው ላይ ቢገለጽም፤ በምን ያህል አብላጫ ድምጽ የሚለው አለመካተቱን አስረድተዋል።
የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በበኩላቸው የደንበኛቸው ያለ መከሰስ መብታቸው የተነሳው እርሳቸው በህግ ቁጥር ስር ከዋሉ በኋላ ቢሆንም፤ በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ “በአካል እንደተገኙ ተደርጎ” በቃለ ጉባኤው ላይ ተጠቅሶ መመልከታቸውን ለችሎቱ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ዮሃንስ እና አቶ ክርስቲያን፤ የስልክ ልውውጣቸው “ከህግ ውጪ የተጠለፈው” ያለ መከሰስ መብታቸው ከመነሳቱ በፊት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በተጨማሪነት ገልጸዋል። በእነዚህ ምክንያቶች የቀረቡባቸውን ማስረጃዎች ውድቅ በማድረግ ችሎቱ “በነጻ እንዲያሰናብታቸው” የጠየቁት ሁለቱ ተከሳሾች፤ “የህግ ጥሰት በፈጸሙ” አካላት ላይ ምርመራ ተጣርቶ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ትእዛዝ እንዲሰጥም አመልክተዋል።
ዐቃቤ ህግ “የስልክ ጠለፋ” እንዲደረግ ያስፈቀደበትን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲያቀርብ እንዲደረግ ሁለቱ ተከሳሾቹ ዛሬም ችሎቱን በድጋሚ ጠይቀዋል። ሁለቱ ተከሳሾች ከሳምንት በፊት በነበረው የችሎት ውሎ፤ የግል የስልክ ልውውጣቸው “ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጠለፉን” ገልጸው፤ ድርጊቱ በህጉ መሰረት ስለመፈጸሙ እንዲረጋግጥላቸው አቤት ብለው ነበር።
ይህንን በተመለከተ ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ በሰጠው ምላሽ፤ የተከሳሾችን የስልክ ልውውጦች ለመጥለፍ ያስፈቀደበትን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሚያቀርብ ገልጿል። ነገር ግን ያለመከሰስ መብት የነበራቸው የምክር ቤት አባላት ላይ የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ምላሽ መጠየቁን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ፤ ተከሳሾቹ በዐቃቤ ህግ ማስረጃ ላይ የሰጡት የጽሁፍ ምላሽን በተመለከተ ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበውን አስተያየት ለመስማት ለመጪው ሳምንት ሐሙስ ጥር 28፤ 2018 ቀጠሮ ሰጥቷል። ካለመከሰስ መብት ጋር በተያያዘ በተላለፉ የምክር ቤት ውሳኔዎች ላይ ለቀረቡት አቤቱታዎች፤ የዐቃቤ ህግ ምላሽ “ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም” የሚለውን መርምሮ በቀጣዩ ችሎት ትዕዛዝ እንደሚሰጥም ችሎቱ ገልጿል።
በዛሬው የችሎት ውሎ በዚህ መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው እና በእስር ላይ ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች መካከል አስራ አምስቱ በአካል ተገኝተው የፍርድ ሂደቱን ተከታትለዋል። በችሎቱ ያልተገኙት አቶ አማረ መለስ የአዕምሮ ህመም የገጠማቸው በመሆኑ እና ተከሳሹ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና እንዲያገኙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠበቃቸው ጠይቀዋል።
ጥያቄውን የተቀበለው ችሎቱ፤ ተከሳሹ ያሉበትን ሁኔታ እና የህክምና ሂደት እንዲያሳውቅ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል። በአማራ ክልል ካለው የጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በእነ አቶ ዮሃንስ መዝገብ ስር የሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ብዛት 52 ነው። አቶ ዘመነ ካሴ እና እስክንድር ነጋን ጨምሮ የ36ቱ ተከሳሶች ጉዳይ የሚታየው በሌሉበት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































