የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ሰሜን ምስራቅ ድንበር ከዚህ ቀደም ከተቆጣጠሩት አካባቢ “የበለጠ ዘልቀው” እንደገቡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ አስታወቁ። በድንበር አካባቢዎች የነበሩ “የባለፉት ጥቂት ቀናት” እንቅስቃሴዎች፤ የኤርትራ መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል የበረታውን ውጥረት “የበለጠ የሚያባብስ መንገድ እንደመረጠ” እንደሚጠቁሙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ይህን የገለጹት ለኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳሌህ ትላንት ቅዳሜ ጥር 30፤ 2018 በጻፉት ደብዳቤ ነው። በማህበራዊ የትስስር ገጾች የተሰራጨው ይህ ደብዳቤ፤ ትክክለኛ እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች አረጋግጣለች።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ ደብዳቤያቸው፤ ሁለቱ ሀገሮች በሚዋሰኑበት የኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ድንበሮች የኤርትራ ወታደሮች ከአማጺ ቡድኖች ጋር “ጥምር ወታደራዊ እንቅስቃሴ” በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። ይህ የኤርትራ ኃይሎች እንቅስቃሴ እና በሰሜን ምስራቅ ድንበር “የበለጠ ዘልቀው” መግባታቸው፤ “ትንኮሳዎች ብቻ ሳይሆኑ ቀጥተኛ ጥቃት ናቸው” ሲሉ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን በኤርትራ መንግስት ላይ ጠንካራ ቃላት ያዘለ ደብዳቤ ሲጽፉ የመጀመሪያቸው አይደለም። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባለፈው ጥቅምት ወር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ “አክራሪ” ያሉት የህወሓት “አንጃ” እና የኤርትራ መንግስት፤ በኢትዮጵያ ላይ “ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጁ ይገኛሉ” ሲሉ ከስሰው ነበር።
ሚኒስትሩ በትላንትና ደብዳቤያቸውም፤ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ “የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ቀጥተኛ የቁሳቁስ ድጋፍ እና እገዛ ሲሰጥ ቆይቷል” ሲሉ ወንጅለዋል። ይሁንና የትኞቹ ታጣቂ ቡድኖች ከኤርትራ መንግስት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በደብዳቤያቸው በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ በፓርላማ በቀረቡበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ “አንዳንድ የህወሓት ሰዎች” ከኤርትራ መንግስት ጋር “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንስራ” እንዳሉ ወንጅለው ነበር። አብይ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ ከኤርትራ መንግስት ጋር የነበራቸው ጸብ “ተፋፍሞ ሄዶ” “የመጨረሻ ጫፍ” ላይ የደረሰው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም እንደነበር ገልጸዋል።
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በጥቅምት 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት፤ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመ ነው። ለሁለት ዓመት በቆየው ጦርነት ወቅት፤ የኤርትራ ወታደሮች ከፌደራል ኃይሎች ጋር በአጋርነት ተሰልፈው ነበር።
ዶ/ር ጌዲዮን በትላንቱ ደብዳቤያቸው፤ ከትግራይ ጦርነት በኋላ በሁለቱ ሀገሮች የድንበር አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ግዛት የኤርትራ ጦር ለረዥም ጊዜ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጥቅምት ወር ለተመድ ዋና ጸሀፊ በጻፉት ደብዳቤ ላይም፤ የኢትዮጵያ ግዛት መያዝ ጉዳይን አንስተው ነበር።
የኤርትራ ጦር ከያዘው የኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ መንግስታቸው ያቀረበው ጥሪ ሰሚ እንዳላገኘ ዶ/ር ጌዲዮን በትላንቱ ደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኤርትራ መንግስት ወታደሮቹን “በአፋጣኝ” ከኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲያስወጣ እና ከአማጽያን ጋር የሚያደርጋቸውን “ሁሉንም አይነት ትብብሮች” እንዲያቆም በደብዳቤያቸው በይፋ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነቱ እንዲከበር ያቀረበውን ጥያቄ ጨምሮ ከኤርትራ “አዎንታዊ ምላሽ” ካገኘ፤ የሁለቱን ሀገራት “የጋራ ጥቅሞች” በተመለከቱ “ሁሉም ጉዳዮች ላይ” ለመደራደር ፈቃደኛ እንደሆነም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል። ዶ/ር ጌዲዮን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሊደረግ የሚችለው ድርድር “የማሪታይም ጉዳዮች” እና የአሰብ ወደብን እንደሚጨምር ጠቁመዋል።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ማክሰኞ በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ “በባሌም ሆነ በቦሌ እንደማይቀር” ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አድርገው ነበር። አሰብ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የገነባቸው “ወደብ፣ ኤርፖርት፣ መንገድ እና የነዳጅ ማጣሪያ” እንዳለ በዚህ ንግግራቸው ያስታወሱት አብይ፤ እነዚህን ሀብቶቹን መልሶ መውሰድ የሚችልበት አካሄድ እንዳለ ጥቆማ ሰጥዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ንግግርም ሆነ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ደብዳቤ በኤርትራ በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ እስካሁን የለም። ሆኖም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ከአንድ ሳምንት በፊት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት “አላስፈላጊ” እና “ሊቀር የሚችል “ግጭትን የሚያስነሳ እንደሆነ አስጠንቅቀው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































