የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን እንዲመሩ ተሾሙ

በቤርሳቤህ ገብረ

በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን ለስድስት ዓመት ገደማ የካቤኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው የሰሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) እንዲመሩ በፓርላማ ተሾሙ። አቶ ብርሃኑ የብሔራዊው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት፤ ተቋሙን ለአምስት ዓመታት የመሩትን ዶ/ር ዳንኤል በቀለን በመተካት ነው።

ዶ/ር ዳንኤል ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱት፤ የስራ ዘመናቸው ባበቃበት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ነበር። ላለፉት አምስት ወራት ኢሰመኮን የመምራት ኃላፊነት በተጠባባቂነት ተረክበው የቆዩት የእርሳቸው ምክትል የነበሩት ራኬብ መሰለ ናቸው።

ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ኢሰመኮ፤ ለሰብዓዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የመስራት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ነው። በ2012 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት፣ በምክትል ዋና ኮሚሽነርነት እና በዘርፍ ኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ ኃላፊዎች በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ይደነግጋል። 

ተሿሚዎች የሚመለመሉት በዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ እንደሆነም በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ሰፍሯል። በዚህ መሰረት የተወካዮች ምክር ቤት ተሰናባቹን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር የሚተኩ ዕጩዎች ለመቀበል ጥቆማ መቀበል የጀመረው ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

ዛሬ ሐሙስ ጥር 22፤ 2017 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ ኮሚቴው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር እንዲሆኑ አቶ ብርሃኑ አዴሎን በዕጩነት አቅርቧል። ላለፉት አስር አመታት በግል አማካሪነት እና ጠበቃነት እየሰሩ የቆዩት አቶ ብርሃኑ፤ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የሰሩ ናቸው። 

አቶ ብርሃኑ በፌደራል ደረጃ የካቤኔ ጉዳዮች ኃላፊ ከመሆናቸው አስቀድሞ፤ በቀድሞው ደቡብ ክልል የፍትህ ቢሮ በሶስት የኃላፊነቶች ቦታዎች ላይ ሰርተዋል። የደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ የአስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት አቶ ብርሃኑ፤ መስሪያ ቤቱን በምክትል እና በዋና ኃላፊነት መርተዋል። የአቶ ብርሃኑ የትምህርት ዝግጅት ይመሩት ከነበረው ቢሮ ስራ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።    

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ያገኙት አቶ ብርሃኑ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ህንድ ከሚገኘው አሊጋህ ሙስሊም ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ዘርፍ ይዘዋል። የኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ ኮሚሽኑን ለመምራት በዕጩነት ለሚቀርቡ ግለሰቦች በመመዘኛነት ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል፤ “በህግ ወይም አግባብ ባለው ሌላ ሙያ የሰለጠነ ወይም በልምድ ሰፊ ዕውቀት ያካበተ” የሚለው ይገኝበታል። 

ብሔራዊውን የሰብአዊ መብት ተቋም ለመምራት የሚወዳደሩ ዕጩዎች፤ “የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ” መሆን እንደሚገባቸውም በአዋጁ ላይ ተደንግጓል። አቶ ብርሃኑ ለአራት ዓመታት ያህል በዋና ዳይሬክተርነት የመሩትን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በታህሳስ 2007 ዓ.ም ከተሰናበቱ በኋላ፤ በግል ስራቸው ላይ መቆየታቸውን ለፓርላማ በቀረበው የትምህርት እና የስራ ልምድ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)