ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ጀምሮ ሊካሄድ ነው

ላለፉት አራት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ፤ ከአንድ ወር በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።  ከሐምሌ 8፤ 2018 በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ለ15 ቀናት በሚካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ አራት ሺህ ሰዎች እንደሚሳተፉ ኮሚሽኑ ገልጿል። 

ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚጀመርበትን ቀን አስመልክቶ ዛሬ አርብ ምሽት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያን ጨምሮ 8 ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን በዚሁ መግለጫ ላይ እንዳሉት ቀጣዩ እና “ዋነኛው” ተግባር፤ “እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ መመካከር እና ዘላቂ መግባባት ላይ መድረስ ነው”። “በውጤቱም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮቻችን ተፈትተው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጽኑ መሰረት እንጥላለን ብለን እናምናለን” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ አጀንዳ እንዲሆኑ ከተጠየቁ ጉዳዮች መካከል “የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት ላይ ማሻሻያ ይደረግ” የሚለው አንዱ ነው። የማንነት ጥያቄ፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ አጠቃቀም፣ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ እና የድንበር አከላለል ጉዳዮችም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች በተካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የተነሱ የምክክር ጉዳዮች ናቸው።

ምክክሩን የሚያካሄዱት ከ12 ክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከፌደራል ባለ ድርሻ አካላት የተወከሉ ተሳታፊዎች፤ ሀገር አቀፍ ጉባኤው ከሚጀመርበት አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ወደ አዲስ አበባ ከተማ “ተጠቃልለው እንዲገቡ” ይደረጋል ተብሏል። ይህ የሚደረገው “አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ምክክር ተግባራትን ለማከናወን” እንደሆነ ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።

በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 1,234ቱ መሳተፋቸውን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አመልክቷል። ይህም ከሀገሪቱ ቦታዎች 93 በመቶ የሸፈነ እንደሆነ ኮሚሽኑ ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)