በ2019 በጀት ለዕዳ ክፍያ የተመደበው ገንዘብ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ሆነ 

የፌደራል መንግስት ለ2019 በጀት ዓመት ካዘጋጀው ጠቅላላ በጀት ውስጥ 542.1 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን፤ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ዕዳ ክፍያ እንዲውል መደበ። ይህ የገንዘብ መጠን በዘንድሮው በጀት ዓመት ለተመሳሳይ ጉዳይ ከተመደበው በ79 ቢሊዮን ብር ገደማ ያሻቀበ ነው።

በመጪው ሐምሌ ወር ለሚጀምረው የ2019 በጀት ዓመት፤ የፌደራል መንግስት ያዘጋጀው የበጀት መጠን 2.34 ትሪሊዮን ብር ነው።  ይህ በጀት ሲዘጋጅ ታሳቢ ከተደረጉ “ዋና ዋና ጉዳዮች” መካከል በ2019 “ሊኖር የሚችለውን የሀገር ውስጥ ብድር ጫና” አንዱ መሆኑ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የበጀት ማብራሪያ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። 

በዚህም ምክንያት በጀቱ ሲዘጋጅ “የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያን ግምት ውስጥ ማስገባቱን” ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው የበጀት ማብራሪያ ጥራዝ አመልክቷል። በ2019 በጀት “ከፍተኛ ድርሻ” የያዘው መደበኛ ወጪ ዝርዝር ሲዘጋጅም የዕዳ ክፍያ ጉዳይ “ታሳቢ መደረጉም” በተጨማሪነት ተገልጿል። 

የፌደራል መንግስት ለመጪው በጀት ዓመት መደበኛ ወጪ የመደበው የገንዘብ መጠን 1.23 ትሪሊዮን ብር ነው። ከመደበኛ ወጪ ውስጥ 43.3 በመቶ ድርሻን በመያዝ ቀዳሚ የሆነው፤ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያ የተመደበው 542.1 ቢሊዮን ብር ነው። 

ግማሽ ትሪሊዮን ብር የተሻገረው ይህ የገንዘብ መጠን፤ ዘንድሮ ለተመሳሳይ ጉዳይ ከተበጀተው ጋር ሲነጻጸር በ17 በመቶ ጨምሯል። በ2019 በጀት ዓመት ለውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን 293.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን ለሀገር ውስጥ ዕዳ የተያዘው ደግሞ 248.7 ቢሊዮን ብር ነው።

በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት አጠቃላይ ዕዳ 52.75 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው የመጪው ዓመት በጀት ማብራሪያ ያሳያል። ከዚህ ውስጥ 64.4 በመቶው የውጭ ዕዳ እንደሆነ በዚሁ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።  

የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ክምችት በ2014 እስከ 2015 በጀት ዓመታት “መጠነኛ ቅናሽ አሳይቶ” እንደነበር የሚገልጸው ይኸው ሰነድ፤ በ2017 በጀት ዓመት “ጭማሪ” ማሳየቱን ያስረዳል። ጭማሪው የተመዘገበው በበጀት ዓመቱ “በበጀት ድጋፍ መልክ የተገኘው የውጭ ሀብት ፍሰት” በማደጉ እንደሆነ ሰነዱ ያብራራል።

“የጭማሪው ምክንያቶችም በዋናነት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራውን ለመደገፍ ከልማት አጋሮቻችን በተለይም ከአይ.ኤም.ኤፍ እና ከዓለም ባንክ የኮንሴንሽናል ብድሮች መለቀቃቸው ነው” ሲል ሰነዱ ያብራራል። ይህን ተከትሎም በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 29.6 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ዕዳ ክምችት፤ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 34 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። 

የበጀት ማብራሪያ ሰነዱ፤ የሀገር ውስጥ ዕዳ ክምችትም “ከዓመት ወደ ዓመት ድርሻው እየጨመረ መምጣቱን” አመልክቷል። በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ከጠቅላላ ዕዳ ክምችት ውስጥ የሀገር ውስጥ ዕዳ ይዞ የነበረው ድርሻ 57.4 በመቶ ነበር።

ይህ ከፍተኛ ድርሻ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ “ወደ 35.6 በመቶ ወርዷል”። ለዚህ በምክንያትነት በሰነዱ የተጠቀሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ማሻሻያ ነው። 

ማሻሻያው ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለውን የምንዛሬ ተመን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው የበጀት ማብራሪያ ሰነድ የዘንድሮውን ዓመት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባይጠቅስም፤ እስከ መጋቢት 2018 በነበረው ጊዜ ብቻ እንኳ መጠኑ በቀደመው በጀት ዓመት ከነበረው መጨመሩን የገንዝብ ሚኒስቴር ሪፖርት አመልክቷል። 

መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት፤ እስከ እስከ መጋቢት 22፤ 2018 ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ብድር መጠን 51.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቆ ነበር። ከዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ የውጭ ብድር የያዘው 33.5 ቢሊዮን ዶላር ያህሉን ነው።

በ2019 ለዕዳ ክፍያ የተመደበው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን፤ ኢትዮጵያ ካለባት የዕዳ ክምችት መሸፈን የሚችለው 6.5 በመቶ ገደማውን ብቻ ነው። ይህም ሆኖ ግን ለዕዳ ክፍያ የተመደበው ገንዘብ፤ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከፌደራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ዝርዝር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሆኗል።  

የዕዳ ክፍያን ተከትሎ በሁለተኛነት የተቀመጠው፤ “ለበጀት ድጋፍ” የተመደበው 238.1 ቢሊዮን ብር ነው። በተመደበለት የገንዘብ መጠን በ2018 የበጀት ድልድል አራተኛ ደረጃን ይዞ የነበረው የትምህርት ዘርፍ፤ በ2019 በጀት ዓመት ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። መጪው ዓመት ለትምህርት ዘርፍ የተያዘው የወጪ መጠን 158.2 ቢሊዮን ብር ነው። 

“ለመጠባበቂያ” ወጪ የተያዘው 124.4 ቢሊዮን ብር በአንጻሩ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በመገባደድ ላይ ባለው የ2018 በጀት “ለመጠባበቂያ” ወጪ የተመደበው 269 ቢሊዮን ብር ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ነበር።

በ2019 በጀት ዓመት አምስተኛ ደረጃን የያዘው የመንገድ ግንባታ ወጪ ነው። ለመጪው ዓመት ለመንገድ የተመደበው የገንዘብ መጠን 123.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ለዘርፉ የተመደበው የገንዘብ መጠን ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በ28.8 ቢሊዮን ብር ከፍ ቢልም፤ በ2018 ባለው አምስተኛ ደረጃው ላይ ግን ለውጥ አላመጣም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)