በኢትዮጵያ በሚከሰቱ በግጭቶች ምክንያት ነጋዴዎች “ለግድያ”፣ “ለስደት” እና “ለንብረት ውድመት” መጋለጣቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ ተናገሩ። በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ሳቢያ በክልሉ የሚገኙ ነጋዴዎች ከባንኮች ተበድረው ያልመለሱት የገንዘብ መጠን ወደ 90 ቢሊዮን ብር ማሻቀቡም ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 10፤ 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በካሄዱት የውይይት መድረክ ላይ ነው። “በሀገራዊ የምክክር ሂደት የግሉ ዘርፍ ያለው ተሳትፎ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የዛሬው ውይይት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ባለፉት ሳምንታት ከተለያዩ አካላት ጋር ሲያደርገው የቆየው ውይይት ቀጣይ መሆኑ ተገልጿል። ኮሚሽኑ በእነዚሁ ጊዜያት በሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በተመለከተ ከሲቪክ ማህበረሰብ፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እና ሌሎችም አካላት ጋር ግምገማዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤውን ከመጪው ሐምሌ 8 ጀምሮ እንደሚያካሄድ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ በዛሬው ውይይቱ ከኢትዮጵያ እና የክልሎች የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አመራሮች ጋር መክሯል። በዚህ ውይይት ላይ የሰላም እና ደህንነት ባለሙያዎችም ተገኝተዋል።
በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት የክልሎች ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ተወካዮች፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮች የንግዱን ማህበረሰብ “በዋናነት” እየጎዳ መሆኑንም ተናግረዋል። ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ መዘግየቱ ችግሩ እንዲባባስ እንዳደረገውም አመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ፤ በኢትዮጵያ ባሉ ግጭቶች ምክንያት ነጋዴዎች “ለንብረት ውድመት፣ ስደት እና ግድያ አደጋዎች መጋለጣቸውን” ገልጸዋል። ነጋዴዎቸ ለዘመናት ያፈሯቸው ንብረቶች “በአንድ ጀምበር እየወደሙባቸው”፣ “ሲሰደዱ” እና ሲፈናቀሉ” ማየታቸውንም በማሳየነት አንስተዋል።
“ዝርፊያው የሚፈጸምበት ነጋዴው ነው። ከባንኮች በ30/70 ብድር ወስዶ የተበደረው እና ያፈራው ሀብት ይወድማል። ከባንኮች የእርሻ ብድር ወስደው የተበላሸ ብድር በሚል ብድራቸው የሚሰረዝላቸው ሰዎች ባሉበት፤ እነሱ ፈቅደው ባላመጡት ጦርነት ብዙ ነጋዴዎች ዛሬ ደህይተዋል”
“ዝርፊያው የሚፈጸምበት ነጋዴው ነው። ከባንኮች በ30/70 ብድር ወስዶ የተበደረው እና ያፈራው ሀብት ይወድማል። ከባንኮች የእርሻ ብድር ወስደው የተበላሸ ብድር በሚል ብድራቸው የሚሰረዝላቸው ሰዎች ባሉበት፤ እነሱ ፈቅደው ባላመጡት ጦርነት ብዙ ነጋዴዎች ዛሬ ደህይተዋል። ጦርነት በፈጠረው ዳፋ ሀብት የነበራቸው ሰዎች ንብረታቸውን አጥተው ቅጠሩኝ የሚሉ ሰዎችን አውቃለሁ” ሲሉ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ በሰላም እጦት ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለማስቀረት የሚያስችል ስርዓት ሊኖረው እንደሚገባም አቶ ቦጋለ ጠቁመዋል። “ራሳችን የምቆጣጠረው፣ ሰላም የምናስጠብቅበት፣ ጦርነት የሚያፋፍም ነጋዴን የምናወጣበት፣ ሰላም እንዲሰፍን የሚሰራውን የምናበረታታበት ራሳችን የምናስተዳድረው ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል” እንደሚያስፈልግም አቶ ቦጋለ ተናግረዋል።
አቶ ቦጋለ በዚሁ አስተያየታቸው፤ በኢትዮጵያ ፖሊሲዎች እና ህጎች ቶሎ ቶሎ መለዋወጣቸውን በተጨማሪ ችግርነት ጠቅሰዋል። ይህ አካሄድ “ኢኮኖሚው ተገማች እንዳይሆን እና ነጋዴዎች ዘላቂ ኢንቨስትመንትን እንዳያስቡ” ማድረጉንም ገልጸዋል።

“የእኛ ሀገር የቁጥጥር ስርዓት ተገማች አይደለም። ብዙዎቹ ‘confidence’ የላቸውም። እርግጠኝነት የለውም። ነገ ምን አይነት ህግ ወጥቶ እንደሚያድር አናውቅም። በህጎች ላይ ጠንካራ የምክክር መድረክ የለም። አብዛኞቹ ለይስሙላ የሚደረጉ ናቸው። ንግድ ምክር ቤት በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል። በዚህ በማይገመት ከባቢ ውስጥ ዘላቂ ኢንቨስትመንትን ማሰብ ከባድ ነው” ሲሉም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል የሆኑት አቶ በሪሁ ሀብቱ በበኩላቸው እርሳቸው በመጡበት በትግራይ ክልል ያሉ ነጋዴዎችን በመወከል ያለባቸውን ችግር አሰምተዋል። በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት በክልሉ ያለው የንግዱ ማህበረሰብ እስከ ሙሉ ውድመት የደረሰ ጉዳት ቢደርስበትም “በቂ ድጋፍ እንዳልተደረገለት” አቶ በሪሁ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ያሉ ነጋዴዎች ከባንኮች ተበድረው ያልከፈሉት ገንዘብ መጠን ወለድ እና ቅጣቱን ጨምሮ ከነበረበት 32 ቢሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት ወደ 90 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አቶ በሪሁ በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኘው የንግድ ማህበረሰብ ብድርን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች እንዲያደርግ ላለፉት ሶስት ዓመታት ቢጠየቅም “በቂ ምላሽ” እና “ድጋፍ” አለመደረጉን ተወካዩ ተችተዋል።
“በትግራይ የመገለል እና የመገፋት ነገር አለ። ጦርነቱ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ነው። በጦርነቱ ከተጎዱት መካከል በህግ የሚመራው የንግዱ ማህበረሰብ ዋነኛው ነው። አሁን ላለው ችግር ኢትዮጵያ መፍትሄ ካልሰጠች ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን እንዴት ነው መፍትሄ የሚሰጠው? ይህ ችግራችን ባልተፈታበት መልኩ ለሀገር ሰላምና ደህንነት አስተዋጽኦ እንዴት ማድረግ እንችላለን?” ሲሉ አቶ በሪሁ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ፤ የሰላም ችግሮችን ጨምሮ ነጋዴዎች የሚያነሷቸው ጉዳዮች በፌደራል እና ክልል መንግስታት ትኩረት እንዲያገኙ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ማንኛውም አይነት የሰላምና መረጋጋት ችግር ሲያጋጥም የግል ተቋማት የመጀመሪያው ተጠቂዎች በመሆናቸው፤ የወከልነው ማህበረሰብ የሚያነሳቸው የዘላቂ ሰላም ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ይገባናል” ብለዋል ዋና ጸሀፊው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ካሉት ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር አምባዬ ኦጋቶ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት ባካሄዳቸው የውይይት መድረኮች ከተሳተፉ 126 ሺህ ግለሰቦች መካከል 14 ሺህ ያህሉ ነጋዴዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከወረዳዎች ጀምሮ በተካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል “በሰላም ተንቀሳቅሶ የመስራት” እንዲሁም “ንብረት የማፍራት መብት ይከበር” የሚለው እንደሚገኝበት ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

የሀገር አቀፉ ምክክር ጉባኤ መዘግየትን በተመለከተ ከዛሬው የውይይት ተሳታፊዎች ለተነሳው ጥያቄው ዶ/ር አምባዬ ምላሽ ሰጥተዋል። ጉባኤው የዘገየው “መተማመንን ለመጨመር” እና “አካታችነትን ለማስፈን” ውይይቶችን ከታችኛው ማህበረሰብ በተለይም ከወረዳ መጀመር አስፈላጊ ነው ተብሎ በኮሚሽኑ በመታመኑ እንደሆነ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 1,234ቱ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ መሳተፋቸውን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም። ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ እነዚህን ወረዳዎች ጨምሮ ከተለያዩ ቦታዎች የተወከሉ አራት ሺህ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























