የመንግስት ገቢን “በከፍተኛ ደረጃ” ማሳደግ “የሞት የሽረት ጉዳይ ነው” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናገሩ  

በቤርሳቤህ ገብረ

የፌደራል መንግስት የሚሰብሰበውን ገቢ በሚቀጥለው ዓመት “በከፍተኛ ደረጃ” ለማሳደግ ማቀዱ “የሞት የሽረት ጉዳይ ነው” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። በኢትዮጵያ ያለውን የልማት ፍላጎት ከአሁን በኋላ ማሳካት የሚቻለው ገቢን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ “አዲስ የልማት ጥያቄ ለመፍታት ብለን ከብሔራዊ ባንክ የምንበደርበት ሁኔታ አብቅቶለታል” ብለዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 24፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። የዛሬው መደበኛ ስብሰባ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው፤ የፌደራል መንግስት ለ2018 ባዘጋጀው በጀት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ነበር። 

የፌደራል መንግስት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለፓርላማ ያቀረበው የበጀት መጠን 1.93 ትሪሊዮን ብር ሲሆን ከሀገር ውስጥ ምንጮች ለመሰብሰብ ያቀደው የገንዘብ መጠን 1.23 ትሪሊዮን ብር ነው። በቀጣዩ በጀት ዓመት ከታክስ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 1.1 ትሪሊዮን ብር ገቢ፤ ለዘንድሮ በእቅድ ከተያዘው በ200 ቢሊዮን ብር ገደማ ጭማሪ አለው።

የ2018 በጀትን አስመልክቶ በዛሬው የፓርላማ ውይይት ላይ ማብራሪያ ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፤ የፌደራል መንግስት የሀገር ውስጥ ገቢን “በከፍተኛ ደረጃ” የማሳደግ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል። መንግስት በአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ የሚያገኘውን የገቢ መጠን በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት “ሀገር ውስጥ ካለ የገንዘብ እንቅስቃሴ” በፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት እንደሚበደር አቶ አህመድ አብራርተዋል። “ስንበደር በአዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ነው የምንበደረው። ከበፊቱ ወደድ ያለ ነው የሚሆነው። ስለዚህ መንግስት እንደ ከዚህ በፊቱ በቀላሉ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚበደርበት አብቅቶለታል” ሲሉም ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ምንም አይነት የልማት ጥያቄ እንኳ ቢኖር ያንን የልማት ጥያቄ ፋይናንስ ማድረግ የምንችለው፤ በዘላቂ የፋይናንስ መርህ ላይ ተመስርተን ነው። አዲስ የልማት ጥያቄ ለመፍታት ብለን ከብሔራዊ ባንክ የምንበደርበት ሁኔታ አብቅቶለታል። አዲስ የልማት ጥያቄ ለመፍታት ብለን በቀላል interest rate ከኢኮኖሚው ውስጥ የምንበደርበት ሁኔታ አብቅቶለታል ማለት ነው። አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ የሚባለው ይሄ ነው። አዲስ ፊሲካል ፖሊሲ የሚባለው ይሄ ነው” ሲሉ አቶ አህመድ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። 

“ምንም አይነት የልማት ጥያቄ እንኳ ቢኖር ያንን የልማት ጥያቄ ፋይናንስ ማድረግ የምንችለው፤ በዘላቂ የፋይናንስ መርህ ላይ ተመስርተን ነው። አዲስ የልማት ጥያቄ ለመፍታት ብለን ከብሔራዊ ባንክ የምንበደርበት ሁኔታ አብቅቶለታል”

– አቶ አህመድ ሽዴ፤ የገንዘብ ሚኒስትር

የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ “የተረጋጋ የሚሆነው” እና “እድገት የሚቀጥለው”፤ ገቢን “በከፍተኛ ደረጃ” በማሳደግ እንደሆነ የገለጹት አቶ አህመድ፤ ይህ ጉዳይ ለፌደራል መንግስት “የሞት የሽረት” እንደሆነ አስገንዘበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰበስበው ታክስ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ጋር ያለው ጥመርታ (ratio) ከብዙ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር አሁንም “ዝቅተኛ” መሆኑን ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ መንግስት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ይሄንን በአራት በመቶ የማሳደግ እቅድ እንዳለው አመልክተዋል።   

የቀጣዩ ዓመት ታክስ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጋር ያለው ጥመርታ፤ ዘንድሮ ካለው በ1.2 በመቶ ጭማሪ ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለፓርላማ በቀረበው የ2018 በጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። በታክስ ላይ የተጣለውን እቅድ ለማሳካት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመው ግብረ ኃይል “ዝርዝር ውይይት” ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አህመድ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት የተመዘገበው የታክስ አሰባሰብ አፈጻጸም በቀጣዩ ዓመትም “ተጠናክሮ የሚቀጠልበት” እንደሆነ ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት በዘንድሮው በጀት ዓመት ከታክስ እና ቀረጥ ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 900.2 ቢሊዮን ብር ነበር። በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ውስጥ የተሰበሰበው ገቢ 815.3 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።

የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴ ለተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትላንትናው ዕለት ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፤  ከሀገር ውስጥ ገቢ ባለፉት 11 ወራት ለመሰብሰብ የተቻለው 436.48 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ ገቢ የእቅዱን 96.79 በመቶ ያሳካ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 48 በመቶ እድገት ያለው መሆኑን ተናግረዋል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህ ዓመት የሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን ከዚህ ቀደም በነበረ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በገለጸበት ወቅት፤ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ አስነስቶ ነበር። የገቢ መጠኑ ከባለፈው አመት ከፍ ይበል እንጂ፤ ወደ ዶላር ተቀይሮ ቢነጻጸር “የእዚህ አመቱ ገቢ መጠን ያነሰ ነው” በሚል በዚሁ ስብሰባ ላይ ተተችቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)