ለሀገር አቋራጭ የህዝብ እና የጭነት ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች የብቃት ምዘና ዳግም ሊሰጥ ነው 

በቤርሳቤህ ገብረ

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለሀገር አቋራጭ የህዝብ እና የጭነት ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች የዳግም ብቃት ምዘና መስጠት በቅርቡ እንደሚጀምር አስታወቀ። ምዘናውን ተከትሎ የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ፤ በዚህ ዓመት ቁጥሩ የጨመረውን የትራፊክ አደጋ በመቀነስ ረገድ “መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል” የሚል እምነት እንዳለው ሚኒስቴሩ ገልጿል። 

ይህ የተገለጸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 19፤ 2017 ባቀረበበት ወቅት ነው። ሪፖርቱን ለፓርላማው በንባብ ያቀረቡት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ፤ ዳግም ምዘና መስጠት ያስፈለገው የአሽከርካሪነት ስራ “አደጋን ተከላክሎ ከማሽከርከር እና የመንገድ ደህንነትን በላቀ ደረጃ ከማስጠበቅ አኳያ ያለበትን ደረጃ” እንደገና ለማረጋገጥ በማስፈለጉ እንደሆነ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

ይህንን በጋር ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ገልጸዋል። በሚኒስቴሩ በተቋቋመ ቡድን አማካኝነት ጥናት ከተካሄደ በኋላ የስራ ደረጃ፤ ስርዓተ ትምህርት እና የስልጠና ማኑዋል መዘጋጀቱን ተናግረዋል። 

“የአሽከርካሪነት ስራ occupational standard እንደሌለው ያወቅነው፤ ይህን ስራ ለመስራት ስንገባበት ነው” ያሉት ዶ/ር አለሙ፤ በአሁኑ ወቅት ለስራው የሚያስፈልግ 40 ሞጁል ስታንዳርድ መዘጋጀቱን አስረድተዋል። ከእነዚህ ሞጁሎች ውስጥ አስራ አምስቱ ለህዝብ ትራንስፖርት፣  አስሩ ደግሞ ለደረቅ እና ፈሳሽ ጭነት ትራንስፖርት የተዘጋጁ መሆናቸውንም አብራርተዋል። 

“እኛ ዝም ብለን ፈተና ብቻ አዘጋጅተን፣ ፈትነን፤ መንጃ ፈቃድ [ለመስጠት] ነበር ያሰብነው። ግን ወደ ስራ ሲገባ ይሄ ፕሮሲጀር እንደሚያስፈልግ ህጉ ያስገድዳል። ደረጃውን የጠበቀ ምዘና ለማድረግ እነኚህ እነኚህ መሟላት አለባቸው። ይሄንን ጨርሰናል። አሁን ምዘና ወደ ማዘጋጀት ተገብቷል” ሲሉ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ አመልክተዋል።

መስሪያ ቤቱ ምዘናውን የሚያደርገው ከዚህ ቀደም እንደነበረው “ስህተት በማይፈጥር ደረጃ” መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሂደቱ በሚኒስትሮች “በቅርብ ክትትል እየተመራ፣ ከሰዎች ንክኪ ነጻ በሆነ እና ማንም በምንም መልኩ አድሎ መስራት የማይቻልበት” መልኩ የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል። 

“የመንጃ ፈቃድ ራሱን፣ የምንሰጠውን የብቃት ማረጋገጫ ራሱን እንቀይረዋለን። ከፋይዳ ጋር እናያይዘዋለን። ለኮፒ እና ለፎርጀሪ በማያጋልጥ መልኩ እናደርጋለን ማለት ነው። በሌላ በኩል ተመሳስሎ የተሰራ ማስረጃ መያዝ በማይችሉበት ሁኔታ እናደርገዋለን” ዶ/ር አለሙ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የወደፊት እቅድ ጠቁመዋል።

የብቃት ማረጋገጫ የሚጀመረው፤ ሚኒስትሩ የትራፊክ አደጋ “ዋና አድራሾች” እና በጅምላ ሰው የሚጨርሱ” ሲሉ ከጠሯቸው የጭነት መኪናዎችን እና አውቶብሶች አሽከርካሪዎች ነው። ለአሽከርካሪዎች እንደሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ሁሉ የተሽከርካሪ መለያ ቁጥርን የተመለከቱ ተመሳሳይ ስራዎች  እየተከናወኑ መሆናቸውንም አክለዋል። 

በኮንትሮባንድ ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች ፎርጂድ ታርጋ እንደሚሰራ የገለጹት ዶ/ር አለሙ፤ ይህንንም “የመቀየር ስራ ነው እየተሰራ” መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በስራ ላይ ሲውል መኪና ሰርቆ፣ ታርጋ ቀይሮ መንዳት አንደማይቻል እና ከባለመኪናው ቁጥጥር ውጪ በሚሆን ሲስተም የታሰረ መሆኑን አስረድተዋል። 

“መኪናዋን ያቃጥላት ይሆናል ወይ  ቅርጫ ያደርጋት ይሆናል እንጂ፤ በዚያ ታርጋ ወይም ቀይሮ መንዳት አይቻልም” ሲሉ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ እነዚህ ለውጦች የትራፊክ አደጋ በመቀነስ ረገድ “መሰረታዊ ለውጥ ያመጣሉ” የሚል ተስፋቸውን በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው አንጸባርቀዋል። 

“እንዲህ እያደረግን እና የህዝብ ተሳትፎ እየጨመርን በመሰረታዊነት የትራፊክ አደጋን የመቀየር ስራ ካልሰራን፣ አደጋው እንዲሁ ይቀጥላል ማለት ነው። ግን ይሄ ስራ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን” ሲሉ ዶ/ር አለሙ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚደርሰው የትራፊክ አደጋ  70 በመቶ የሚጠጋው “በአሽከርካሪ ስህተት” የሚከሰት እንደሆነ ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)