የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን፤ በአዲሱ የደመወዝ ማስተካከያ ጭማሪ መሰረት “የመስከረም ወር ክፍያ አልተፈጸመልንም” ሲሉ በማህበራቸው አማካኝነት ቅሬታ አቀረቡ። የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው በመረጃ ክፍተት ምክንያት ለፌደራል መንግስት የተላከው የገንዘብ መጠን ጥያቄ ከሚፈለገው በማነሱ እንደሆነ ገልጾ፤ ይህንኑ ለመቅረፍ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ለመንግስት ሰራተኞች ከመስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የደመወዝ ማሻሻያ እንደሚደረግ የፌደራል መንግስት ያስታወቀው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበር። ሆኖም የደመወዝ ጭማሪው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች እስከ ህዳር ወር ተግባራዊ ሳይደረግ ዘግይቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ በህዳር መጀመሪያ ላይ በሰጠው መግለጫ፤ በአዲሱ የደመወዝ ማሻሻያ መሰረት የተደረገው ጭማሪ የመስከረም እና የጥቅምት ወር ውዝፍ ክፍያ ከቀናት በኋላ እንደሚፈጸም አስታውቆ ነበር። የክልሉ መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል ጳውሎስ፤ ቢሮው ይህን መግለጫ ከሰጠ በኋላ የጥቅምት ወር ውዝፍ ክፍያ ለመምህራን ቢፈጸምም የመስከረም ወር ግን በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች እስካሁን አለመከፈሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ መምህራን ጥያቄ በማንሳት ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አማኑኤል፤ ችግሩ በቀጠለባቸው የክልሉ አካባቢዎች የትምህርት ማቆም አድማ የማድረግ ሙከራዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። በጋሞ ዞን እና በኮሬ ዞን በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ተነስቶ ከነበረው የደሞዝ ጭማሪው ክፍያ ጥያቄ ጋራ በተገናኘ፤ ትምህርት ከሳምንት በላይ ተቋርጦ አራት መምህራንም ታስረው እንደነበርም አመልክተዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ፤ በሁለት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ውስን አካባቢዎች ለአንድ ሳምንት ያህል መስተጓጎል እንደነበረ አረጋግጠው፤ ችግሩ በንግግር እልባት ማግኘቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከክልሉ መምህራን ማህበሩ እና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋራ በመተባበር በተደረገው ጥረት፤ በውዝፍ የደመወዝ ጭማሪ ክፍያው ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱ “ሳይስተጓጎል” መቀጠሉንም አክለዋል።
“መምህራን ትምህርት ቤት ገቡ ማለት የመማር ማስተማር ሂደቱ በአግባቡ ቀጥሏል ማለት አይደለም” የሚሉት የክልሉ መምህራን ማህበር ሰብሳቢ፤ ችግሩ አፋጣኝ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። ለችግሩ መፍትሔ ለማስገኘት የመምህራን ማህበሩ ከክልሉ ትምህርት እና ፋይናንስ ቢሮዎች ጋራ በቅርበት እየሰሩ እንደሆነ የገለጹት አቶ አማኑኤል፤ ከመንግሥት አካላት ጋራ በተደረሰው መግባባት የታሰሩ መምህራን ተፈትተው ትምህርትም መቀጠሉን አብራርተዋል።

በመምህራን የደመወዝ ክፍያ ላይ ችግር የተፈጠረው፤ ለፌዴራሉ የገንዘብ ሚኒስቴር የተላከው የደመወዝ ጥያቄ ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የመንግስት ሰራተኞች መረጃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ምክንያት ነው ተብሏል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይንናስ ቢሮ ኃላፊ አማካሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ደፋር፤ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በክልሉ ያለውን የሰራተኛ ብዛት ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ መላክ ሲገባው ለመስሪያ ቤታቸው ያስተላለፈው “የ2016 መረጃ” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ለዚህ ክፍተት መነሻ “ከየዞኖቹ የተላከው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ ነው” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ለፌዴራሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንዲሁም የክልሉ የፋይናንስ ቢሮም ለፌዴራል የገንዘብ ሚኒስቴር ይህንኑ መሰረት በማድረግ መረጃ መላካቸውን ጠቅሰዋል። በየዞኖቹ በ“ሕገ-ወጥ” መንገድ የተቀጠሩ ሰራተኞች፤ ክልሉ ያለው የሰራተኞች ብዛት እንዲያሻቅብ ማድረጉንም አክለዋል።
የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ በተደረገው ማጣራት፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለዘንድሮው በጀት ዓመት የ10 ወራት የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 13.7 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል። ሆኖም የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ለገንዘብ ሚኒስቴር አስቀድሞ ያቀረበው የደመወዝ ጥያቄ 7.1 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፤ የ6.6 ቢሊዮን ብር ክፍተት መታየቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

ቢሮው ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አማካሪው፤ በህጋዊም ይሁን በህገ-ወጥ መንገድ ለተቀጠሩት የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች ከመስከረም ወር ውጪ ያለው ክፍያ መፈጸሙን አስረድተዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል፤ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ለዞኖች እና ወረዳዎች ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት የተወሰኑ መዋቅሮች ለመምህራን ቅድሚያ እየሰጡ ክፍያ በመፈጸም ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም መሰረት ሶስት የሪጂዮ ፖሊስ ከተማ አስተዳደሮች ትላንት ሐሙስ ታኅሣሥ 9፤ 2018 የመምህራንን ውዝፍ የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ “ሙሉ በሙሉ ከፍለው ማጠናቀቃቸውን” አቶ አማኑኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሪጂዮ ፖሊስ ደረጃ ያላቸው ወላይታ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ እና ዲላ ከተሞች ናቸው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ 12 ዞኖች ውስጥ የወላይታ ዞን “ሙሉ በሙሉ” እና የጋሞ ዞን ደግሞ በከፊል የመስከረም ወር ውዝፍ የደመወዝ ጭማሪ ለመምህራን መክፈላቸውን አቶ አማኑኤል ገልጸዋል። ቀሪዎቹ 10 ዞኖች የመስከረም ወር ውዝፍ የደመወዝ ጭማሪ እስካሁን ድረስ እንዳልከፈሉ የክልሉ መምህራን ሰብሳቢ አክለዋል።

በክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች የመስከረም ወር ክፍያ ያልተፈጸመው፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ጭማሪውን መላክ የጀመረው ከጥቅምት ወር ጀምሮ በመሆኑ እንደሆነ የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ተስፋዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሶዶ ክላስተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ፤ ክፍያቸውን ያጠናቀቁት አካባቢዎች በራሳቸው አቅም ካመነጩት ገቢ ወስደው እንደሆነም ገልጸዋል።
የደመወዝ ጭማሪውን በዚህ መልክ የከፈሉ መዋቅሮች፤ ችግሩ ሲቀረፍ ከቢሮው የሚመለስላቸው መሆኑንም አማካሪው አመልክተዋል። ችግሩን ለመቅረፍም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋራ “በተደረገው መግባባት”፤ የክልሉን የመንግስት ሰራተኛ ትክክለኛ ቁጥር፣ የሚያስፈልገውን የበጀት መጠን እና የመስከረም ወር የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ጥያቄን ቢሮው ከቀናት በፊት ለመስሪያ ቤቱ መላኩን አስረድተዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ምላሽ በመጠባበቅ ላይ” መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ከአሁኑ የውዝፍ ደመወዝ ጭማሪ በተጨማሪ በተደጋጋሚ የደመወዝ ክፍያ አለመፈጸም ጥያቄዎች ከሚነሱባቸው ክልሎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም ምክንያት መምህራንን ጨምሮ የተለያዩ የሲቪል ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማዎችን ማድረጋቸው እና በዚህም ሳቢያ እስር እና የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውም አይዘነጋም። ከደመወዝ ክፍያ ጋራ በተገናኘ ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሄዱን የሚናገሩት የክልሉ መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል፤ ያለፈው ዓመት ከ2016 ዓ.ም “የተሻለ ነበር” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































