የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለንግድ እና ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውሉ 220 ቦታዎችን ለሊዝ ጨረታ አቀረበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ ለሚያከናውነው የመሬት ሊዝ ጨረታ፤ የሰነድ ሽያጩን ከመጪው ሰኞ ታህሳስ 27፤ 2018 ጀምሮ ለተከታታይ አስር ቀናት እንደሚያካሄድ አስታወቀ። አስተዳደሩ ለዚህ ዙር ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት 220 ነው።

ለንግድ ወይም ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውሉት እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት፤ በየካ፣ በጉለሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በለሚ ኩራ፣ በቂርቆስ፣ በአዲስ ከተማ፣ በልደታ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች እንደሆነ ተገልጿል። በአሁኑ ጨረታ የአራዳ እና የቦሌ ክፍለ ከተሞች አልተካተቱም።

ለአሁኑ ጨረታ የቀረቡት በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች የሚገኙት ቦታዎች፤ አጠቃላይ ስፋታቸው 7.7 ሄክታር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል። ቦታዎቹ “ከፕላን ተቃርኖ እና ከይገባኛል የጸዱ መሆናቸውንም” ቢሮው አመልክቷል። 

ፎቶ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ

ባለፈው ጥቅምት ወር በተደረገው ተመሳሳይ የመሬት ሊዝ ጨረታ፤ ከአርሶ አደር መብት፣ ከፍርድ ቤት እግዶችና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ምክንያቶች 110 የሚሆኑት መሬቶች ከሂደቱ ውጭ መደረጋቸው የሚታወስ ነው። በእዚህ ዙር ለሊዝ ጨረታ ቀርበው የነበሩ ቦታዎች ብዛት 384 ነበር።

ለእነዚህ ቦታዎች ከቀረቡ ዋጋዎች ውስጥ ከፍተኛው መጠን የተመዘገበው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነው። በክፍለ ከተማው ለሚገኝ 100 ካሬ ሜትር ቁራሽ መሬት፤ አሸናፊው ተጫራች በካሬ ሜትር የሰጡት ዋጋ 135,000 ብር ነበር። 

ይሄ የገንዘብ መጠን ባለፈው ነሐሴ ወር በተከናወነው ጨረታ በካሬ ሜትር ቀርቦ ከነበረው 91,330 ብር ከፍተኛ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በ43,670 ብር የጨመረ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቆመውን የመሬት ሊዝ ጨረታ እንደገና ማውጣት በጀመረበት በግንቦት 2015 ዓ.ም. ለአንድ ካሬ ሜትር የተሰጠው ከፍተኛ ዋጋ 695,000 ብር ደርሶ ነበር።

ፎቶ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ

የሊዝ ጨረታ ዋጋ “እንደወቅቱ” እና “እንደገበያው ፍላጎት” የሚለዋወጥ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የጨረታ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክብሮም አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የመሬት ሊዝ ጨረታዎች ላይ “የዋጋ መረጋጋት” እንዳለ የገለጹት አቶ ክብሮም፤ ይህም ሊሆን የቻለው ቢሮው በተከታታይ እያወጣ ባለው ጨረታ ትክክለኛ ቤት ፈላጊዎች እራሳቸው በመጫረታቸው እና ከደላላ የሚገዙበት ሁኔታ እየቀነሰ በመምጣቱ መሆኑን አስረድተዋል።

በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ቢሮው 80 ሄክታር የሚሆን ስፋት ያለው መሬት በጨረታ ለማውጣት እቅድ መያዙን ያስገነዝቡት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ባለፉት ሁለት ዙሮች ብቻ 20 ሄክታር መሬት ለጨረታ መቅረቡን አመልከተዋል። በዚሁ ዓመት ከጥር ወር በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ቢሮው ሶስት ተጨማሪ የመሬት ሊዝ ጨረታዎችን የማውጣት እቅድ እንዳለውም አክለዋል።

ለጨረታ እየቀረቡ ያሉ መሬቶች በምን መልኩ ተመርጠው እንደሚዘጋጁ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ክብሮም፤ “አዲስ አበባችን ሰፊ ናት። በከተማው በየመሀሉ ኪስ መሬቶች አሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮው ጨረታ ሲያወጣ በተለይ በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ፎቶ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ

የአርሶ አደር መሬት ካለ “ካሳ ተከፍሎበት” ለጨረታ ሊወጣ እንደሚችል የጠቆሙት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ በመሬት ባንክ ውስጥ ያሉ መሬቶችም በየጨረታዎቹ እንደሚካተቱ አብራርተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ለልማት” የተፈለጉ ቦታዎችን ካሳ በመክፈል ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ ሲያደርግ መቆየቱንም አቶ ክብሮም አስታውሰዋል።

በ2011 ዓ.ም. የከተማ መሬትን በሊዝ ለመያዝ የወጣው አዋጅ፤ የከተማ ቦታ በሊዝ የሚያዘው፤ በጨረታ ወይም በምደባ ስልት እንደሆነ ይደነግጋል። ተሻሽሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የእዚህ አዋጅ ረቂቅ ሰነድ ደግሞ ከእነዚህ ስልቶች በተጨማሪ በድርድር መሬትን ለማስተላለፍ የሚፈቅድ ድንጋጌን እንዲጨመር አድርጓል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ሊዝ ጨረታ እንደገና ማውጣት ከጀመረበት ከግንቦት 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሰባት ዙር ጨረታዎችን አከናውኗል። አስተዳደሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት ካካሄዳቸው ሁለት የሊዝ ጨረታዎች “2.3 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን” አቶ ክብሮም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)