የከተማ መሬትን በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው

በቤርሳቤህ ገብረ

የከተማ መሬትን ከጨረታ እና ከምደባ በተጨማሪ በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው። አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት መሬት መጠን ውስጥ፤ ቢያንስ 20 በመቶውን ለቤት ግንባታ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል። 

“የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ” እንደወጣ የተገለጸው ይህ አዋጅ፤ ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 19፤ 2017 በሚካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ አጀንዳ ተይዞለታል። በ2004 ዓ.ም የጸደቀውን “የከተማ ቦታን ስለመያዝ የወጣ አዋጅን” የሚተካው አዲሱ የህግ ረቂቅ፤ በስድስት ክፍሎች እና በ49 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው። 

የአዋጅ ረቂቁ የመጀመሪያ ክፍል አጠቃላይ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ መሰረታዊ የሊዝ ድንጋጌዎችን ይዘረዝራል። የከተማ መሬት ሊዝ ጨረታ አፈጻጸም ዝርዝር ጉዳዮች በአዋጁ ሶስተኛ ክፍል ተካትተዋል። 

የከተማ መሬት በምደባ እና በድርድር፤ በሊዝ ስለሚፈቀዱባቸው ሁኔታዎች የሚዘረዝሩ ድንጋጌዎች የተቀመጡት በአዋጁ አራተኛ ክፍል ላይ ነው። አምስተኛው የአዋጁ ክፍል የከተማ መሬት ሊዝ አስተዳደርን የሚዳስስ ሲሆን የመጨረሻው የአዋጅ ክፍል ደግሞ ቅጣትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ይዟል።

አዲሱ አዋጅ የተዘጋጀው “በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የከተማ መሬት ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንዲመጣ በማድረጉ፤ ይህንን ፍላጎት በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል የመሬት ሀብት አቅርቦት እና አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ” መሆኑ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። “በነባሩ ህግ ያጋጠሙ የህግ ክፍተቶችን ለማስተካከል እና የሊዝ ስርዓቱን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ማካተት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ” አዲሱን አዋጅ ለማዘጋጀት ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም በሰነዱ ላይ ተቀምጧል። 

በአዋጅ ረቂቁ ከተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች መካከል “መሬትን በድርድር በሊዝ ለማስተላለፍ” የሚፈቅደው ድንጋጌ ይገኝበታል። አስራ ሶስት ዓመት ያስቆጠረው ነባሩ አዋጁ፤ የከተማ ቦታ በሊዝ እንዲያዝ የሚፈቀደው በጨረታ ወይም በምደባ ስልት ብቻ ነበር። በአዲሱ አዋጅ የተካተተው “የድርድር” ስልት፤ “በጨረታ እና በምደባ አግባብ” ለተጠቃሚ ሊተላለፉ በማይችሉ የከተማ መሬቶች ላይ፤ አንድ አልሚ “ለተለዩ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው አገልግሎቶች” መሬት በሊዝ ይዞ ማልማት የሚፈቀድበት ነው። 

ይህ ተግባራዊ የሚደረገው “አግባብ ያለው አካል” ከአልሚዎች ጋር በሚያስቀምጠው “የልማት እቅድ መሰረት” እና “ከአልሚው ጋር በመደራደር” እንደሆነ የአዋጁ የትርጓሜ ክፍል ያስረዳል። የከተማ መሬት በድርድር ሊተላለፍ የሚችለው “ሀገራዊ እና ክልላዊ የከተማ ልማት ስፓሻል ፕላንን” መሰረት በማድረግ እንደሆነም በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ለሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎች፤ መሬት በድርድር አግባብ ሊተላለፍ እንደሚችል በአዲሱ አዋጅ ተደንጓል። በፌደራል መንግስት ለሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለከፍተኛ የትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲሁም ለምርምር ዘርፍ ፕሮጀክቶች የከተማ መሬት በድርድር ሊተላለፍ እንደሚችል በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተዘርዝሯል።   

የአገልግሎት ዘርፉን የሚደግፉ ባለኮከብ ሆቴሎች እና ለቱሪስት ልማት ለሚውሉ ሪዞርቶችም የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎች በድርድር አሰራር ሊስተናገዱ እንደሚችሉ በአዲሱ አዋጅ ላይ ተገልጿል። በግሉ ዘርፍ አሊያም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ በሽርክና ሊለሙ የሚችሉ የከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶችም፤ በዚሁ የመሬት አሰጣጥ አግባብ እንደሚስተናገዱ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ለሪል ስቴት ወይም ለቤት ልማት የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎች፣ የግዙፍ የገበያ ማዕከላት (ሞል) ፕሮጀክቶች፣ ትላልቅ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች እና ማከፈፋያዎች፣ ለዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ህንጻ ግንባታዎች የሚውሉ ቦታዎች፤ በተመሳሳይ መልኩ በድርድር ማግኘት እንደሚቻልም በአዲሱ አዋጅ ላይ ተመልክቷል። 

በድርድር አግባብ የሚስተናገዱ ፕሮጀክቶች “የሚመጣዉ ልማት ይዘት፣ ስፋትና ጥልቀት፤ ለልማት በተመረጠው ቦታ ነባር ተጠቃሚ የሆኑ ባለይዞታዎች መስተንግዶና ተጠቃሚነት፣ በዙሪያ ባሉ ማህበረሰቦች ተጠቃሚነትና ጉዳት ቅነሳ እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ድርሻ” ከግምት ውስጥ እንደሚገባ የአዋጅ ረቂቁ አትቷል።

የከተማ ቦታ በድርድር አግባብ እንዲተላለፍ የሚደረገው፤ በክልሎች፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አስተዳደሮች “ካቢኔ ሲወሰን ብቻ” እንደሆነም አዲሱ አዋጅ ያስቀምጣል። መሬት በድርድር የማስተላለፊያ ዋጋ፤ ከአካባቢው አማካይ የሊዝ ጨረታ ዋጋ በታች መሆን እንደሌለበትም በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል። 

በምደባ ስለሚሰጥ የከተማ መሬት በነባሩ አዋጅ ላይ ተዘርዝረው የነበሩ ድንጋጌዎች፤ ለፓርላማ በቀረበው የአዋጅ ረቂቅ በከፊል ተካትተዋል። ሆኖም አዲሱ አዋጅ፤ “ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል የመሬት የአቅርቦት ሁኔታን” የተመለከተ አዲስ ድንጋጌ በውስጡ እንዲይዝ ተደርጓል። 

አዲሱ ድንጋጌ “ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት የመሬት መጠን” ውስጥ “ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን” ለቤት ግንባታ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል። በአንድ ከተማ በመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበር፣ በጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም ወይም በተናጠል የከተማ መሬትን በምደባ ተጠቃሚ የሆነ ግለሰብ፤ በዚያው ከተማ “ለሁለተኛ ጊዜ በምደባ ተጠቃሚ እንዳይሆን” የሚያግድ አዲስ ድንጋጌም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተካትቷል።

በአዲሱ አዋጅ፤ መሬት በጨረታ የሚያሸነፉ ግለሰቦች ለሚያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች ላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል። እስካሁን በስራ ላይ ባለው የሊዝ አዋጅ፤ አንድ ተጫራች የመሬት ጨረታ አሸናፊ የሚሆነው፤ ባቀረበው የጨረታ ዋጋ እና የቅድመ ክፍያ መጠን ላይ ተመስርቶ በሚደረግ ስሌት ከፍተኛውን ነጥብ ሲያገኝ ነው።

በአዋጅ ረቂቁ ላይ ይህ ተቀይሮ፤ የሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች የሚለዩት፤ ከጨረታ ዋጋ እና የቅድሚያ ክፍያ በተጨማሪ የሊዝ ክፍያ ማጠናቀቂያ ጊዜ ተሰልቶ በሚገኘው የድምር ውጤት ነው። በአዲሱ አዋጅ የጨረታ ዋጋ 65 በመቶ፣ የቅድሚያ ክፍያ 20 በመቶ እና የሊዝ ክፍያ ማጠናቀቂያ 15 በመቶ ነጥብ እንደሚኖራቸው ተብራርቶ ተቀምጧል።  

አዲሱ አዋጅ ከዚህ በተጨማሪ የሊዝ መነሻ ዋጋ የሚከለስበትን ጊዜ ከሁለት ዓመት ወደ ሶስት ዓመት ከፍ አድርጎታል። “የሊዝ መነሻ ዋጋ” ማለት ዋና ዋና የመሰረተ-ልማት አውታሮች የመዘርጊያ ወጪን፣ ነባር ግንባታዎችና ንብረቶችን ለማንሳት የሚያስፈልገውን ወጪና ለልማት ተነሺዎች የሚከፈል ካሳአን እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መስፈርቶች ታሳቢ ያደረገ የመሬት ዝቅተኛ ዋጋ ነው።

ረቂቅ አዋጁ የመሸጋገሪያ ድንጋጌን በዘረዘረበት ክፍሉ፤ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት አግባብ ላለው አካል ለቀረቡ የከተማ መሬት ጥያቄዎች የሚሆን አንቀጽ አስቀምጧል። እነዚህ ጥያቄዎች አዋጁ ከጸናበት ቀን ጀምሮ እስከ ስድስት ወራት ድረስ፤ በነባሩ አዋጅ እና አዋጁን መሰረት አድርገው በወጡ ደንብ እና መመሪያዎች ውሳኔ የሚያገኙ እንደሚሆን ሰነዱ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)