በጋምቤላ ክልል የጸጥታ መደፍረስ “ተሳትፎ ነበራቸው” የተባሉ 62 የፖሊስ አባላት ጉዳይ በህግ እየታየ መሆኑ ተገለጸ

በጋምቤላ ክልል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ወቅት “በጥፋት ድርጊቶች ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው ተረጋግጧል” ከተባሉ 272 የፖሊስ አባላት ውስጥ የ62ቱ ጉዳይ በህግ እየታየ መሆኑን አንድ የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ 642 የፖሊስ እና የአድማ ብተና አባላትን ከስራ ማሰናበቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ ፖሊሶች ላይ ይህን እርምጃ የወሰደው፤ ሁሉንም ያካተተ የተሃድሶ ስልጠና እና ግምገማ ካደረገ በኋላ መሆኑን ገልጿል። በጋምቤላ ክልል ከተከሰተው የጸጥታ ችግር በኋላ በክልሉ ያሉ የመደበኛ ፖሊስ አባላት እና የአድማ ብተና ፖሊሶች የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ የተደረገው፤ በመከላከያ ሰራዊት ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ማሰልጠኛ ነበር። 

ወደ ማሰልጠኛ ተቋሙ ላልገቡ ቀሪ የፖሊስ አባላት፤ ኮሚሽኑ “አካላዊ የግምገማ መድረክ” በማዘጋጀት “ሂስ እና ግለሂስ” እንዲያካሄዱ አድርጓል። ይህንን ተከትሎ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ፤ በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ እና የፖሊስ የስነ ምግባር መመሪያ መሰረት “ዝርዝር ግምገማ” ማድረጉ ዛሬ አርብ መጋቢት 18፤ 2018 በተሰራጨ መረጃ ላይ ተመልክቷል። 

የዲስፕሊን ኮሚቴው ባካሄደው ግምገማ፤ በፖሊስ አባላቱ የተፈጸሙ “ጥፋቶችን” መለየቱም ተጠቁሟል። የጥፋት ዓይነቶቹ በዋናነት የሸፈኑት፤ በጸጥታ መደፍረስ ወቅት የተፈጸሙ ጥሰቶችን፣ የጦር መሣሪያ አጠቃቀምን እና የተቋሙን ስርዓት መጣስን ነው።

እንደ ፖሊስ ኮሚሽኑ ገለጻ፤ በግምገማው ወቅት “የተወሰኑ አባላት ለስራ ባልደረቦቻቸው ከለላ ከመስጠት ይልቅ ለግጭት መቀስቀስ ምክንያት ሆነዋል”። እነዚሁ የፖሊስ አባላት “በሕዝብ ላይ ጥይት እስከ መተኮስ የደረሰ ሚና የነበራቸው” እንደሆኑም በግምገማው መለየቱ ተጠቅሷል።

“የጦር መሣሪያ ከህግ ውጭ መጠቀም” እና “በግጭት  ወቅት ጥይት በማጉደል” ጥፋተኛ የተባሉ የፖሊስ አባላትም በግምገማው መለየታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ለጸጥታ ስራ ወጪ ያደረጉትን የጦር መሳሪያ “ገቢ አለማድረግ” እና “ይዞ መጥፋት” ሌላው በግምገማው የተለየ ጥፋት እንደሆነ በኮሚሽኑ መረጃ ላይ ሰፍሯል።

“የመንግስትን ጥሪ ባለመቀበል የታጠቁትን የጦር መሳሪያ ገቢ ያላደረጉ” እና “መሳሪያ አስረክበው ወደ ተሃድሶ ስልጠና ለመሄድ ፈቃደኛ ያልሆኑ” የአድማ ብተና ፖሊስ አባላትም በግምገማው ወቅት በጥፋተኝነት መለየታቸው ተገልጿል። በጋምቤላ ክልል ለሳምንታት ዘልቆ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት፤ ሁሉም የአድማ ብተና እና የመደበኛ ፖሊስ አባላት የታጠቁትን የጦር መሳሪያ እስከ ጥር 7፤ 2018  ገቢ እንዲያደርጉ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር።

የጦር መሳሪያን ገቢ ያለማድረግን ጨምሮ በሌሎችም “የጥፋት ድርጊቶች” ተሳታፊ መሆናቸው “የተረጋገጠ” የፖሊስ አባላት ብዛት 272 መሆኑን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬ መግለጫው ይፋ አድርጓል። ከእነዚህ የፖሊስ አባላት መካከል 62 የሚሆኑ አባላት በክልሉ እና በፌደራል ደረጃ ጉዳያቸው “በሕግ እየታየ” መሆኑን አንድ የኮሚሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል 17ቱ በጋምቤላ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ እና ማስረጃ እየተሰበሰበባቸው እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የኢታንግ እና የአቦል ወረዳዎች ፖሊስ አዛዦች ኧእንደሚገኙበትም ጠቁመዋል። የኢታንግ እና የአቦል ወረዳዎች እንደ ጋምቤላ ከተማ ሁሉ ለሰዎች ህይወት መጥፋት እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መፈናቀል ምክንያት የሆነ የጸጥታ ችግር የተከሰተባቸው አካባቢዎች ነበሩ። 

በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩ የፖሊስ አባላት መካከል “ማስረጃ ያልተገኘባቸው” በዋስ እንዲወጡ መደረጉንም ኃላፊው አክለዋል። ማስረጃ የተገኘባቸው አባላት በበኩላቸው ጉዳያቸው በጋምቤላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ  መደረጉንም አስታውቀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ጉዳያቸው በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ የተያዘ የክልሉ መደበኛ ፖሊስ እና የአድማ ብተና አባላት ብዛት 45 ነው። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኡጉላ ኡጁሉ እንደሚገኙበት ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

አቶ አጉላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለቤታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። የቀድሞው ፖሊስ ኮሚሽነር  በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዘው ወደ ቤታቸው ለፍተሻ ከመወሰዳቸው አስቀድሞ በጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደነበሩ ባለቤታቸው በወቅቱ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው ዕለት ባሰራጨው መረጃ፤ የጋምቤላ ክልል “ጥቂት የፖሊስ አመራር እና አባላት” በክልሉ ተከስቶ የነበረውኝ የጸጥታ መደፍረስ ችግርን በሕግ አግባብ ከመከላከል እና ከመቆጣጠር ይልቅ “በጸረ-ሰላም ኃይሎች ሴራ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ሆነዋል” ሲል ወንጅሏል። የክልሉ ፖሊስ አመራር እና አባላት “በብሔርተኝነት፣ በጎሰኝነት እና በብልሹ አሰራር ውስጥ” መገኘታቸውንም ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ ለደረሰው “የሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት” እነዚሁ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት “ሚና እንደነበራቸው” በተደረገው ግምገማ “መረጋገጡንም” ገልጿል። በጋምቤላ ክልል ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተው ግጭት እና “የጸጥታ መደፍረስ”፤ “የሰዎች ህይወት መጥፋቱን” እና “የአካል ጉዳት መድረሱን” የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታወቆ ነበር።  

ይህንኑ የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ፤ የክልሉ ዋና መቀመጫ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ ጨምሮ “የጸጥታ ችግር ይስተዋልባቸዋል”በተባሉ አካባቢዎች ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ ቆይቷል። የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ይፋ ባደረገው የጊዜ ገደብ መሰረት፤ በከተማይቱ የሚገኙ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽት 1 ሰዓት ብቻ ነበር። 

በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች እና ግሮሰሪዎችም አገልግሎት መስጠት የሚችሉት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ መሆኑን አስተዳደሩ በዚሁ ወቅት አስታውቆ ነበር። የጋምቤላ ከተማን የጸጥታ ሁኔታ የገመገመው የከተማይቱ ኮማንድ ፖስት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ ሆቴሎች ፣ ሱቆችና ተሽከርካሪዎች እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት  ድረሰ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ውሳኔ አስተላልፏል።

በጋምቤላ ከተማ አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆችም፤ የሰዓት እላፊ ገደባቸው እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ እንዲሆን ማሻሻያ አድርጓል። በከተማይቱ የሞተር ሳይክል የሚያሽከርከሩ ግለሰቦች ላይ “ላልተወሰነ ጊዜ” የተጣለው ገደብ ግን ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)