ምርጫ ቦርድ፤ መጪውን ምርጫ በግንቦት 28 ሊያካሂድ ነው

  • የደቡብ ምዕራብ ክልል ህዝበ ውሳኔ በተመሳሳይ ቀን ይካሄዳል
  • በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ድምጽ የሚሰጠው በሰኔ 5 ይሆናል
  • ለትግራይ ክልል የተለየ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ይዘጋጃል

በተስፋለም ወልደየስ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የመጪውን ምርጫ እና የደቡብ ምዕራብ ክልል ህዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጫ ቀንን በተመሳሳይ ቀን ሊያደርግ ነው። ከትግራይ ክልል፣ ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ውጪ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርጫ የሚካሄደው በግንቦት 28፤ 2013 እንደሚሆን ቦርዱ ዛሬ ይፋ ባደረገው ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አስታውቋል። 

በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ያሉ መራጮች ድምጽ የሚሰጡት፤ ከሳምንት በኋላ ሰኔ 5፤ 2013 እንደሚሆን የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ አመልክቷል። ቦርዱ የምርጫውን የመጨረሻ ውጤት ይፋ የሚያደርገው ከምርጫው ማግስት ጀምሮ እስከ ሰኔ 21፤2013 ድረስ ባሉት ጊዜያት እንደሆነም ተገልጿል። 

ዛሬ አርብ ታህሳስ 16 ለፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ የትግራይ ክልልን እንደማይጨምር ቦርዱ አስታውቋል። ቦርዱ በክልሉ በክልሉ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የተለየ የጊዜ ሰሌዳ ወደፊት እንደሚያዘጋጅ ገልጿል። 

“በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምርጫ በሚስማማ መልኩ መመቻቸቱ ሲረጋገጥ በክልሉ የሚደረገውን ምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ቦርዱ የሚያስታውቅ ይሆናል” ብሏል ቦርዱ።

ለትግራይ ክልል ብቻ የሚሆን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ካስፈለገባቸው መክንያቶች አንዱ ቦርዱ “የምርጫ ቢሮዎችን ለመክፈት የክልል መስተዳድር አካላት ከፍተኛ ትብብር ስለሚያስፈልገው እና የክልሉ ጊዜያዊ መንግስት ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ጊዜ ስለሚያስፈልገው” እንደሆነ ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)