በተስፋለም ወልደየስ
በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በእርቀ ሰላም ስብሰባ ላይ በነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የልዩ ወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በዛሬው ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ የልዩ ወረዳው የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና አንድ ፖሊስ እንደሚገኙበት የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የእርቀ ሰላም ስብሰባው የተጠራው፤ በአማሮ ልዩ ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲከሰት ለነበረው ግጭት መቋጫ ለማበጀት በማሰብ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በሁለቱ አካባቢዎች አዋሳኝ ቦታ ላይ በምትገኘው ዳኖ ቀበሌ ላይ እየተካሄደ የነበረው ይህ ስብሰባ፤ ገና ከመጀመሩ በታጣቂዎች ተኩስ መቋረጡን በቦታው የነበሩ ዓይን እማኝ አስረድተዋል።
ስብሰባውን ራቅ ብለው ሲከታተሉ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ተካበ ገነነ የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ፤ የተኩስ እሩምታ የተሰማው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ እንደነበር ይገልጻሉ። የአማሮ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወገኔ ደጀኔ የመክፈቻ ንግግር እያሰሙ ባለበት ወቅት፤ ስብሰባው በሚካሄድበት ቦታ አቅራቢያ ባለ ጫካ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ ታጣቂዎች በመውጣት ተኩስ መክፈታቸውን ያብራራሉ።
የዓይን እማኙ ከነበሩበት ቦታ ሆነው የታጣቂዎቹን ማንነት በግልጽ መለየት አለመቻላቸውን ቢናገሩም፤ የእርሳቸውም ሆነ የሌሎች ነዋሪዎች ግምት ግን በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት “የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው” የሚል ነው። የአማሮ ልዩ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ለጥቃቱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል።
“የካቲት 29፤ 2013 ዓ.ም. በአማሮ ወረዳ እና በምዕራብ ጉጂ ዞን አጎራባች ቀበሌያት መካከል ሠላማዊ ስብሰባ እየተካሄደ በነበረበት ቦታ፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በታጠቀው በሸኔ ኦነግና በታጣቂው ቡድን በከፈተው እና በተተኮሰው ጥይት የብዙሃን ህይወት አልፏል” ሲል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
በጥቃቱ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን የገለጸው ጽህፈት ቤቱ፤ ከሟቾቹ ውስጥ የልዩ ወረዳው አመራር እና ፓሊስ እንደሚገኝበት ጠቁሟል። በጥቃቱ የተገደሉት አመራር፤ የልዩ ወረዳው የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ኤቼላ መሆናቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዛሬው ጥቃት በጠና ቆስለው ሆስፒታል ከገቡ ስድስት ሰዎች ውስጥ የልዩ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ወገኔ ደጀኔ እንደሚገኙበት የዓይን እማኞች ጨምረው ገልጸዋል። የልዩ ወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት በጥቃቱ “በርከት ያሉ ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል” የሚል ማረጋገጫ ቢሰጥም፤ ስለተጎጂዎቹ ማንነትም ሆነ ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ግጭቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመሩት ባለፉት አራት ዓመታት እንደሆነም ያስረዳሉ።
የአማሮ ልዩ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን ጥቃት የሚፈጽሙት “ሸኔ እና አጋሮቹ ናቸው” ሲል ይወነጅላል። በእነዚህ ታጣቂዎች በየጊዜው በሚፈጸሙ ጥቃቶች “ከመቶ በላይ ሰዎች ሞተዋል። ብዙ ቀበሌያት ወድመዋል” ሲል ጽህፈት ቤቱ በዛሬው መግለጫው ከስሷል። የዛሬውን ጥቃት በተመለከተ ከአካባቢው ባለስልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነውን ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)