በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት በትግራይ ክልል የጋራ ምርመራ ለማድረግ ተስማሙ። ሁለቱ ተቋማት የሚያከናውኑት ምርመራ፤ በክልሉ በነበረው ግጭት በሁሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ ማጣራት የሚያደርግ ነው።
ኢሰመኮ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ምርመራውን በመነሻነት ለማከናወን የተስማሙት ለሶስት ወራት ያህል ነው። ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣውና በክልሉ ምርመራውን የሚያከናውነው ቡድን “በተቻለ ፍጥነት በቅርቡ” ወደ ስፍራው እንደሚንቀሳቀስም ኮሚሽኑ ገልጿል።
በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ከጥቅምት 24 ጀምሮ፤ ተቋማቱ በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ እንደነበር ያስታወሰው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ከክልሉ የሚወጡ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በደሎችን የያዙ ሪፖርቶች “አሁንም እንደሚያሳስቧቸው” አትቷል። በክልሉ ያለው ግጭት በሰላማዊ የክልሉ ህዝብ ላይ ያስከተለው ውድመትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚመለከቱት አክሏል።
“በግጭቱ በርካታ ተዋናያን በመሳተፋቸው እና በተዘገቡ ጥሰቶች ከባድነት የተነሳ፤ ተጨባጭ እና ነጻ ምርመራ በአስቸኳይ ማድረግ ያስፈልጋል” ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው።
መንግስታዊው ተቋም ኢሰመኮ እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የጋራ ምርመራ ለማድረግ የተስማሙት፤ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ቀደም ሲልም ጀምሮ በነበረው አጋርነት እና ትብብር መሰረት ነው ተብሏል። ድርጅቶቹ እንዲህ አይነት ምርመራዎች የሚያከናውኑት ባላቸው ስልጣን መሰረት መሆኑም ተገልጿል።
የተመድ የሰብዓዊ መብት ተቋም በትግራይ ክልል ምርመራ ለማካሄድ የተስማማው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለምርመራው ፍቃደኝነቱን መግለጹን ተከትሎ ነው። የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚሼል ባሽሌት ለጋራ ምርመራው “አዎንታዊ ምላሽ” የሰጡት ባለፈው ሳምንት ነበር። ኮሚሽነሯ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጡት መግለጫ በትግራይ “የጦር ወንጀል ሳይፈጸም አይቀርም” ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)