“ጎል” የተሰኘው የአየርላንድ የግብረ ሰናይ ድርጅት አንድ ሰራተኛ በምዕራብ ወለጋ ዞን መገደላቸውን ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ሰራተኛው የተገደሉት ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በአሶሳ እና ያሶ መካከል በሚገኝ ቦታ መሆኑን ገልጿል።
የግብረ ሰናይ ድርጅቱ በዛሬው መግለጫው እንዳለው፤ ጥቃቱን የፈጸሙት ማንነታቸው ያልታወቀ 12 ታጣቂዎች ናቸው። ታጣቂዎቹ በጉዞ ላይ የነበረ የድርጅቱን መኪና ካስቆሙ በኋላ ሾፌሩን እና የድርጅቱን ሰራተኛ አግተው ወደ ጫካ መውሰዳቸውንም አመልክቷል።
“[ሰራተኞቹ] በጥቃት ፈፃሚዎቹ ጥያቄ ከተጠየቁ በኋላ፤ አሽከርካሪው በጥይት ተመቶ ሲገደል የጎል ሰራተኛ ለማምለጥ ችሏል” ብሏል “ጎል” በመግለጫው። “ፈታኝ በሆነ ከባቢ ውስጥ የተቸገሩ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን ለመርዳት ሥራቸውን በሚያከናውኑ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ የተፈጸመውን ይኸን ግድያ አጥብቀን እናወግዛለን። ይህ ጥቃት በትዕግስት ሊታለፍ አይገባም” ሲል ለሟች ቤተሰቦች ሀዘኑን በገለጸበት መግለጫ አውግዟል።
ጥቃት የደረሰባቸው ሰራተኞች ወደ ስፍራው የተጓዙት በአካባቢው የሚፈለገውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታ ለመገምገም እንደነበር የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጠቁሟል። በኪራይ አገልግሎት ይሰጥ ነበር በተባለው የድርጅቱ ተሽከርካሪ፤ የዕርዳታ ድርጅቱ መለዮ፤ የሚለጠፍ ባንዲራ እና የጦር መሳሪያ እንዳልተጫነበት የሚጠቁም ምልክት እንደነበረው ተቋሙ ገልጿል። ታጣቂዎቹ በተሽከርካሪው ውስጥ የነበረውን ንብረት ከወሰዱ በኋላ በእሳት እንዳጋዩትም መግለጫው አክሏል።
በሰራተኛው ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ተጨማሪ መረጃ እያሰባሰበ እንደሚገኝ የገለጸው የግብረ ሰናይ ድርጅቱ፤ “ግድያው በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች የሚገጥማቸውን አደጋ ያሳያል” ብሏል። ታጣቂ ቡድኖች “የሰብዓዊ ዕገዛ አቅርቦትን ማክበር አለባቸው” ሲልም አሳስቧል።
ጥቃቱን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን በመግለጫው የጠቆመው ድርጅቱ፤ በኢትዮጵያ “የግብረ-ሰናይ ሰራተኞችን ደህንነት እና ጸጥታ ለማረጋገጥ የባለስልጣናቱ እና ማህበረሰቡ አፋጣኝ እርምጃ ያሻል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
ከተመሰረተ 44 ዓመት የሞላው “ጎል”፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ60 ሀገራት የሚንቀሳቀስ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ነው። ላለፉት 37 አመታት ገደማ በኢትዮጵያ የእርዳታ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየው ድርጅቱ፤ በአሁኑ ወቅት በሰባት ክልሎች ተሰማርቶ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)